loading
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሁለትዮሽ ግንኙነት እና የኢኮኖሚ ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፁ::

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 17 ፣ 2013 ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሁለትዮሽ ግንኙነት እና የኢኮኖሚ ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፁ:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ይህን ያሉት ለሁለት ቀናት ወደ ኤርትራ ባደረጉት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ ጋር በአስመራ ውይይት ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው:: ሁለቱ መሪዎች በትግራይ ክልል ከተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ተወያይተዋል:: ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የህወሃት የወንጀል ቡድን በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመሰንዘር ሀገር በማተራመስ ሥልጣን ለመያዝ የከሸፈ ሙከራ ማድረጉን በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልፀዋል::

ቡድኑ ሰሜን እዝን በማጥቃት የመከላከያ አባላትን በጭካኔ በመግደል እና በማፈን በፈፀመው እኩይ ተግባር የፌዴራሉን መንግሥት ወደ ህግ ማስከበር ዘመቻው እንዲገባ አስገድዷል ፡፡ የእዙን ጥቃት ተከትሎ የህወሃት ቡድን በባህር ዳር እና በጎንደር ከተሞች ሮኬቶችን ተኩሷል፡፡ በተመሳሳይም ይህ የህወሃት የወንጀል ቡድን ወደ የኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ሮኮት ተኩሷል::

ይህ ጥቃትም የኤርትራ መንግስት የኢትዮጵያ ድንበር አቋርጦ እንዳይገባ እና ተጨማሪ ጥቃቶችን ለመከላከል እና ብሄራዊ ደህንነቱን ለማስጠበቅ እንዲንቀሳቀስ አድርጏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስመራ ላይ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ ጋር ባደረጉት ውይይትም የኤርትራ መንግስት ጦሩን ከኢትዮጵያ ድንበር ለማስወጣት ተስማምቷል ብለዋል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኃይል የድንበር አካባቢዎችን ለመጠበቅ ስፍራውን ወዲያው ይረከባል ነው ያሉት::

ጠቅልይ ሚኒስትር አቢይ በሁለቱ አጋር ሀገራት መካከል መተማመን እና መልካም የሆነ የጉርብትና መንፈስ መገንባታችንን እንቀጥላለን ብለዋል:: በተለይም ይህን በመተማመን ላይ የተመሰረተ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ድንበር አካባቢ በሚኖሩ በትግራይ ክልል እና ኤርትራውያን ወገኖቻችን መካከል መመለስ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ መረጃው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *