loading
የሕክምና ፍቃድ ሳይኖረው የኮቪድ-19 ሕክምና ሲሰጥ የነበረው ግለሰብ ተያዘ፡፡

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2013 የሕክምና ፍቃድ ሳይኖረው የኮቪድ-19 ሕክምና ማዕከል በመክፈት አገልግሎት እየሰጠ የነበረ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ጃፓን ኤምባሲ አካባቢ በሕገ-ወጥ መንገድ የሕክምና ፍቃድ ሳይኖረው የኮቪድ-19 ሕክምና ማዕከል በመክፈት አገልግሎት እየሰጠ የነበረ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

የአየር መንገድ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ከቦሌ ክፍለ ከተማ የምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ባለሙያዎች ጋር በሰሩት ጥናት ፍቃድ ሳይኖረው ክሊኒክ በመክፈት የኮሮና ቫይረስ ሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ የነበረውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተጣራበት እንደሚገኝ የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ወንጀል ምርመራ ክፍል ገልጸዋል፡፡ በክፍለ ከተማው የወረዳ 2 የምግብ እና መድሀኒት ቁጥጥር ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጦና እንደተናገሩት ፤ግለሰቡ ምንም ዓይነት የሕክምና ፍቃድ ሳይኖረው በራሱ ተነሳሽነት በከፈተው የሕክምና ማዕከል የውጪ ሀገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች ጭምር ሕክምና ፈልገው መምጣታቸውን ገልፀው ነርስ ነን የሚሉ ግለሰቦችም በቦታው ላይ የሕክምና አገልግሎት ሲሰጡ መገኘታቸውን ገልፀዋል፡፡

በወቅቱ በርካታ መድኃኒቶች በቤቱ ውስጥ መገኘታቸውን እና ለምን ዓይነት ሕመም የሚያገለግሉ መድኃኒቶች እንደሆኑም በማጣራት ላይ እንደሚገኙ ኃላፊው ገልጸዋል። ሕገ-ወጥ አገልግሎት የሚሰጡ አካላትን ለሕግ አሳልፎ ከመስጠት አኳያ ህብረተሰቡ የሚያደርገው ትብብር መልካም የሚባል እና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት እንደሆነ ገልጿል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *