የምዕራባውያኑ ሀገራት መሪዎች በኢራን የኒውክሌር ስምምነት ላይ መወያየታቸው ተሰማ።
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2014 የምዕራባውያኑ ሀገራት መሪዎች በኢራን የኒውክሌር ስምምነት ላይ መወያየታቸው ተሰማ። የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ እና የጀርመን መሪዎች የ2015ቱ የኢራን የኒውክሌር ስምምነትን ለማደስ በሚደረገው ጥረት ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን ዋይት ሀውስ እሁድ እለት አስታውቋል።
በዚሁ መግለጫ ሀገራቱ በኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ በመካሄድ ላይ ባለው ድርድር፣ በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ያሉ አጋሮችን ድጋፍ ማጠናከር እና የኢራንን ቀጠናዊ እንቅስቃሴዎችን ለመገደብ በሚደረገው የጋራ ጥረት ላይ መመካከራቸው ተጠቁሟል።
የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካ ባለፈው ሳምንት በቀረበው የመጨረሻ ሀሳብ ላይ የኢራንን ምላሽ እየጠበቁ ነው የተባለ ሲሆን ቴህራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯን ለመግታት ከተስማማች በምላሹ ከተጣሉባት የኢኮኖሚ ማዕቀብ እንደምትላቀቅ ይጠበቃል። የኒውክሌር ድርድሩ አለመሳካት አካባቢያዊ ስጋቱን ከፍ ሊያደርግ ይችላል የተባለ ሲሆን እስራኤል የዲፕሎማሲው ሂደት ቴህራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ አቅም እንዳትፈጥር ካልከለከላት በኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች።
የምዕራባውያኑን ተደጋጋሚ ወቀሳ እና ዘለፋ ለረጅም ጊዜ ስትከላከል የቆየችው ኢራን በበኩሏ ለማንኛውም የእስራኤል ጥቃት በቂ ምላሽ እንደምትሰጥ አስጠንቅቃለች።በ2018 የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኒውክሌር ስምምነቱን ውድቅ ያደረጉት ሲሆን ጠንከር ያለውን የአሜሪካ ማዕቀብ ሲጥሉ ቴህራን በዩራኒየም ማበልፀግ ላይ የነበራትን ገደብ እንድትጥስ አነሳስቷታል ተብሏል።