የሶስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ተካሂደዋል
አርትስ ስፖርት 17/03/2011
በተለያዩ ምክንያቶች እየተቆራረጠ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ፤ በሶስተኛ ሳምንቱ ጥቂት ጨዋታዎች ተካሂደዋል፤ አራት ያህል ግጥሚያዎች ደግሞ ለሌላ ጊዜ ተላልፈዋል፡፡
በሳምንቱ ትናንት ሁለት ጨዋታዎች ሲከናወኑ በደቡብ ደርቢ ሀዋሳ ከተማ ወላይታ ዲቻን አስተናግዶ 2 ለ 1 በመርታት የነጥቡን መጠን ወደ ስድስት ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡ ሁሉንም የፕሪምየር ሊግ ግጥሚያዎችያከናወነው ሀዋሳ አሸናፊ ያደረጉትን ጎሎች እስራኤል እሸቱና ታፈሰ ሰለሞን ሲያስቆጥሩ ፀጋዬ አበራ የድቻን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡
በሌላ ግጥሚያ ሽረ ላይ ስሑል ሽረ አዳማ ከተማን አስተናግዶ 0 ለ 0 በሆነ አቻ ውጤት አጠናቅቀዋል፡፡
ቅዳሜ ዕለት ደቡብ ፖሊስ ሀዋሳ ላይ ከደደቢት ጋር ተጫውቶ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ድል በማድረግ የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ሶስት ነጥብ ማሳካት ችሏል፡፡ በረከት ይስሓቅ ደግሞ የድል ግቧን ማስቆጠር ችሏል፡፡
ዓርብ እለት በሁከት የታጀበው ጨዋታ በሲዳማ ቡና እና ባህር ዳር ከነማ መካከል ተካሂዶ በአንድ አቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡ የሲዳማን ግብ አዲስ ግደይ እንዲሁም የባህር ዳርን ዳንኤል ኃይሉ በፍፁም ቅጣት ምትከመረብ ማገናኘት ችለዋል፡፡
የሊጉን የደረጃ ሰንጠራዥ መቐለ 70 እንደርታ፣ ኢትዮጵያ ቡናና ሀዋሳ ከተማ በእኩል ስድስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ከአንድ እስከ ሶስት ደረጃን በመያዝ ይመራሉ