የባልደራስ እና የምርጫ ቦርድ የችሎት ክርክር::
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 26፣ 2013 ምርጫ ቦርድ ሰበር ችሎት ለባልደራስ የወሰነውን ለምን እንዳልፈጸመ ቀርቦ እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እነ አቶ እስክንድር ነጋ (3 አባላት) በዕጩነት እንዲመዘገቡ የሰጠውን ውሳኔ ለምን መፈጸም እንዳልቻለ የሚያስረዳዉም
ሐሙስ ግንቦት 26 ቀን 2013 ዓ.ም ነዉ፡፡ ፍርድ ቤቱ ለቦርዱ ትዕዛዙን ያስተላለፈው ሰኞ ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ሲሆን፣ ለትዕዛዙ መነሻ የሆነው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ)፣ ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠውን ውሳኔ፣ ቦርዱ ‹‹አልፈጽምም›› ማለቱን ገልፆ፣ እስከሚፈጽም ድረስ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲካሄድ የተወሰነው አገራዊ ምርጫ እንዲታገድለት አቤቱታ በማቅረቡ መሆኑን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡
ፓርቲው ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የምርጫ ጉዳዮች ችሎት ባቀረበው አቤቱታ፣ ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠውን ውሳኔ ቦርዱ ለመፈጸም እምቢተኛ መሆኑን ጠቁሞ፣ ዕጩዎቹ በተወዳዳሪነት ሳይመዘገቡ ድምፅ ቢሰጥ፣ መብቱን በእጅጉ ከመንካቱም በላይ፣ ፍርድ ቤቶች በምርጫ ጉዳይ የሚሰጡት ውሳኔ ‹‹ተፈጻሚነት አይኖረውም›› የሚል ጥርጣሬ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ እንደሚያሳድር በማስረዳት፣ ምርጫው እንዲታገድለት አመልክቷል፡፡ በሌላ በኩል ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠውን ውሳኔ ትክክል እንደሆነና ‹‹መፈጸም አለብህ›› የተባለውን ሙሉ በሙሉ እንደሚቀበለው በመግለጽ፣ ነገር ግን አግባብነት ካላቸው የአገሪቱ የምርጫ ሕግ ማዕቀፍ አንፃር ውሳኔውን ተፈጻሚ ለማድረግ ፍጹም አዳጋች እንደሚሆንበት በመጠቆም፣ የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ለችሎቱ ቀርበው እንዲያስረዱ ጥያቄ አቅርቧል፡፡
አንድን ምርጫ ሁሉን አቀፍ፣ ነፃ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ ከሚያደርጉና ለዜጎች የተረጋገጠውን የመምረጥና የመመርጥ መብት ሙሉ በሙሉ ዕውን ለማድረግ ቁልፍ ጉዳዮች መካከል፣ በሕግ አግባብና ከአድልኦ ነፃ በሆነ ሁኔታ የሚደረግ የዕጩዎች ምዝገባ አንዱ መሆኑን ያብራራው ቦርዱ፣ ነገር ግን የተጠቀሱት ነገሮች የሚከናወኑበትን ሥርዓት የመደንገግ አስፈላጊነት እንደሚገኝበት ማስረዳቱን ሪፖርተር አስነብቧል፡፡