loading
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪዎቹ የሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ይከናወናሉ

ተጠባቂው የሸገር ደርቢ በዚህ ሳምንት መርሀግብር የሚከናወን ሲሆን በዕለተ ሰንበት 10፡00 ሰዓት ላይ በኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል ይደረጋል፡፡

የበርካታ ደጋፊዎች ባለቤቶች ሁለቱ የአዲስ አበባ ክለቦች የዘንድሮው የሊጉ ውድድር የልብ ደጋፊዎቻቸውን ጭምር ያላስደሰተ ጉዞ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

በመጀመሪያው ዙር ያለግብ በአቻ ውጤት መለያየታቸው ይታወሳል፤ አሁን በሊጉ የደረጃ ሰንጠራዥ ፈረሰኞቹ በ37 ነጥብ እና 13 ንፁህ ጎሎች ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ፤ ቡናማዎቹ በ32 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡

ቅዳሜ ዕለት ሶስት ግጥሚያዎች ሲከናወኑ፤ ሁለቱ በክልል ስታዲየሞች ላይ በተመሳሳይ 9፡00 ይደረጋሉ፡፡

የጎንደሩ ፋሲል ከነማ ወደ ትግራይ ክልል በመጓዝ መቐለ ላይ በግዙፉ ስታዲየም የወራጅ ቀጠና ግርጌ ላይ የሚገኘውን ደደቢት የሚገጥም ይሆናል፡፡

ሌላኛው ወራጅ ቀጠና ላይ የሚገኘው ቡድን ደቡብ ፖሊስ ሀዋሳ ላይ አዳማ ከተማን ያስተናግዳል፡፡

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው (ማንጎ)ን ወደ ስራቸው እንዲመለሱ ያደረገው ባህር ዳር ከነማ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ከመከላከያ ጋር ይጫወታል፡፡ የጣና ሞገዶቹ ከ20ኛ ሳምንት የሊጉ መርሀግብር እዚሁ ስታዲየም በኢትዮያ ቡና 5 ለ 0 መረታታቸው ይታወሳል፡፡

እሁድና ሰኞ የ22ኛ ሳምንት የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች ሲቀጥሉ በዕለተ ሰንበት ከሸገር ደርቢ በተጨማሪ ሶስት ግጥሚያዎች በክልል ስታዲየሞች እንዲሁም ሰኞ አንድ የሳምንቱ የማሳረጊያ ግጥሚያ በተመሳሳይ 9፡00 ሰዓት ይደረጋሉ፡

የደቡቡ ክለብ ወላይታ ድቻ ወደ ምስራቅ አቅንቶ፤ ከድሬዳዋ ከነማ ጋር ይፋለማል፡፡

የሊጉ አናት ላይ የተቀመጠው መቐለ 70 እንደርታ በትግራይ ስታዲየም ከስሑል ሽረ ጋር ትልቅ ትንቅንቅ ያለበትን የትግራይ ደርቢ ጨዋታ ያደርጋል፡፡ መቐለ በሊጉ መሪነት ለመግፋት፣ ሽረ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት የሚደረግ ግጥሚያ መሆኑ ጨዋታው ይጠበቃል፡፡

ሀዋሳ ከተማ በደቡብ ደርቢ ከሲዳማ ቡና ጋር ጥሩ ጨዋታ ያደርጋሉ፡፡ ሰኞ ጅማ አባ ጅፋር በትግራይ ስታዲየም ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን ይጎበኛል፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ21 ሳምንታት ጉዞ መቐለ 70 እንደርታ በ45 ነጥቦች ቀዳሚ ነው፤ ፋሲል ከነማ በአምስት ነጥብ አንሶ 40 ነጥብ ሰብስቦ 2ኛ ደረጃን ይዟል፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሲዳማ ቡና እና ጅማ አባ ጅፋር በተመሳሳይ 37 ነጥብ ባለቸው ንፁህ የግብ ክፍያ ከ3- 4 ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *