የከተራ እና የጥምቀት በዓላት ሃይማኖታዊ ትውፊታቸውን ጠብቀው በሰላም እንዲከበሩ ህዝበ ክርስቲያኑ የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ጥሪ አቀረበች።
አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2014 የከተራ እና የጥምቀት በዓላት ሃይማኖታዊ ትውፊታቸውን ጠብቀው በሰላም እንዲከበሩ ህዝበ ክርስቲያኑ የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ጥሪ አቀረበች። የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል እንደ ወትሮው ሁሉ ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ጠብቆ በደመቀ ሁኔታ ለማክበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዝግጅት ማድረጓን በቤተ ክርስቲያኗ የብፁዕ ወ ቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽህፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ የበላይ ኃላፊ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ገልጸዋል። በርካታ ዲያስፖራዎች ወደ አገር ቤት ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ በዓሉን ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ
ደማቅ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል፡፡
ይህ ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል ከሕዝቡ ባህል ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው በመሆኑም ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውም የጎላ መሆኑንም ነውያነሱት። በየዓመቱ በበዓሉ ላይ ለመታደም በርካታ ቱሪስቶች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሲሆን ይህም ለአገሪቱ ኢኮኖሚያ የሚያበረክተው አስተዋጽኦውም ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያዊያን በዓሉን በፍቅር፣ በአንድነት እና በህብረት የሚያከብሩት በመሆኑም በህዝቦች መካከል ማህበራዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለውም ጠቅሰዋል።የዓለም አቀፍ ቅርስ ጭምር የሆነውን ይህ በዓል ህዝበ ክርስቲያኑ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ እና በተረጋጋ ሁኔታ ማክበር እንደሚጠበቅበትም ጥሪ አቅርበዋል ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ።
በተለይ ወጣቶች ሰላምን በማስጠበቅ፣ ስነ-ስርአት በማስያዝና በማስተባበር ከዚህ ቀደም የሚያሳዩትን በጎ ተግባር አሁንም መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ጥንት አባቶች በዓሉ ሐይማኖታዊ ስርአቱንና ትውፊቱን ሳይለቅ ጠብቀው ማቆየታቸውን ጠቅሰው፤የአሁኑ ትውልድም በዓሉ ሐይማኖታዊ ስርአቱን፣ ‘ዶግማና ቀኖናውን’ ጠብቆ እንዲከበር እና ለትውልዱ እንዲተላለፍ የማደረግ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል። የጥምቀት ክብረ በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት በ2012 ዓ.ም መመዝገቡ ይታወሳል።