loading
የደቡብ ዕዝ ወታደራዊ ፍርድ ቤት የዕዙ የሰራዊት አባላት ሆነው ለአሸባሪው ህወሓት ሲሰሩ በነበሩ የሰራዊት አባላት ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 19፣2013 የደቡብ ዕዝ ወታደራዊ ፍርድ ቤት የዕዙ የሰራዊት አባላት ሆነው ለአሸባሪው ህወሓት ሲሰሩ በነበሩ የሰራዊት አባላት ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ የሰራዊት አባላቱ ለህገ-መንግስቱና ለሀገራቸው የገቡትን ቃል ኪዳን ወደጎን በመተው የሰራዊቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች አደጋ ላይ የሚጥሉና የትግራይ ልዩ ሃይልን የሚያጠናክሩ ተግባራትን ሲያከናውኑ መቆየታቸው በችሎቱ ተነስቷል፡፡ በተለይም የሰራዊቱን ልዩ ልዩ ምስጢራዊ ሰነዶች ለትግራይ ልዩ ሃይል አሳልፈው በመስጠት፣ የሰራዊቱን ልዩ ልዩ ትጥቆች የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዳይሰጡ ምስጢራዊ ቡድን በማደራጀትና መሳሪያዎቹን በማበላሸት ስራ ላይ ተጠምደው እንደነበር በችሎቱ ተገልጿል፡፡

በዚህ የተከሳሾች መዝገብ ስር ፤ለግዳጅ የተዘጋጁ መሳሪያዎች የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዳይሰጡ በማድረግ፣ሰራዊቱ ሽብርተኛውን የሸኔ አባላትን ለመደምሰስ በሚንቀሳቀስበት ዕለት ቀድሞ መረጃ በመስጠትና ተልዕኮው ተፈላጊውን ውጤት እንዳያገኝ በማድረግ፣ የሰራዊቱን ምስጢራዊ ክንዋኔዎች
ለሽብርተኛው አካል እንዲደርስ በማድረግ የሚሉ ክሶች ቀርቦባቸዋል፡፡ በተጨማሪም በበላይ አካል የሚሰጣቸውን ተልዕኮ ወደጎን በመተው ከሽብርተኛው አካል የሚሰጣቸውን ድብቅ አጀንዳ መፈፀም በሚያስችላቸው አካሄድ ላይ ብቻ ማተኮር፣ የትግራይ ልዩ ሃይሎች “የብልፅግና ወታደሮችን” ድል እያደረጉ ነው የሚል ሽብር በመንዛት በሰራዊቱ ውስጥ የሚገኙ የትግራይ ተወላጅ የሰራዊት አባላትን በማነሳሳት የቆሙለትን አላማ ወደጎን በመተው የወንጀል ድርጊታቸው አካል እንዲሆኑ በማድረግ፣ ከቆሙለት ሃገራዊ አላማ ይልቅ ለክልል ልዩ ሃይል የሚጠቅሙ ተግባራትን ማከናወን የሚሉ ክሶች ተዘርዝረዋል።

ተከሳሽ የሰራዊት አባላትም የቀረቡላቸውን ክሶች ክደው የተከራከሩ ሲሆን የዕዙ ፍትህ ቡድን የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን አቅርቦ መከራከሩን የዘገበው ኢቢሲ ነው፡፡ ግራ ቀኙን ያዳመጠው ወታደራዊ ፍርድ ቤትም ተከሳሾቹ በቀረቡባቸው ክሶች ላይ በትክክል መከላከል ያልቻሉ በመሆኑ ጥፋተኛ ናቸው ሲል በመወሰን የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *