የግብጹ አስዋን ግድብ አቅራቢያ በመሬት መንቀጥቀጥ መመታቱ ተገለጸ::
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20 ፣ 2013 የግብጹ አስዋን ግድብ አቅራቢያ በመሬት መንቀጥቀጥ መመታቱ ተገለጸ:: በግብጽ አስዋን ግድብ አቅራቢያ በትናንትናው ዕለት የመሬት መንቀጥቀጥ መመዝገቡን የአገሪቱ የአስትሮኖሚ እና ጂዮፊዚክስ ሃላፊን ጠቅሶ ኢጅፕት ኢንድፐንደንት ዘግቧል። የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ከግድቡ ደቡባዊ አቅጣጫ ላይ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ የመሬት መንቀጥቀጡም በሬክተር ስኬል መለኪያ 3 ነጥብ 1 ሆኖ መመዝገቡ ተጠቁሟል።
በዚሁ መሬት መንቀጥቀጥ የጎላ ጥፋት እንዳልተከሰተ ተገልጿል። በግብጽ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች የተከሰቱ ሲሆን፤ በአገሪቱ ታሪክ
ከፍተኛ ጥፋት ያስከተለው እአአ በ1903 የተከሰተውና የ10 ሺህ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው አደጋ መሆኑ ይታወቃል። ግብጾች በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በተለያዩ መንገዶች የሚያሰሙ ሲሆን፤ ከሰሞኑም ግድቡ የሚሰራበት አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ያሰጋዋል ማለታቸው ይታወሳል።
አሁን በመሬት መንቀጥቀጥ በተመታው የግብጹ የአስዋን ግድብ ያለው አመታዊ የውሃ ትነት መጠን ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ በጋራ የመልማት ፍላጎት እና ራዕይ በግብጾች ዘንድ ቢኖር በግብጽ ግድብ ከመገንባት ይልቅ በተፋሰሱ የላይኛው አገራት መገንባት ይበልጥ አዋጭ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮሎጂ ተመራማሪ ዶ/ር ኬቨን የተባሉ ባለሙያ በሰሩት ጥናት መሰረት፤ ግብጽ በአስዋን ግድብ ካከማቸችው የአባይ ውሃ በየአመቱ 10 .9 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ በትነት መልክ ይባክናል። ይህ የውሃ መጠን የአዋሽ ወንዝን ከ2 እጥፍ በላይ የሚበልጥ መሆኑን መረጃዎች
ያሳያሉ።