loading
የፖሊስ ልዩ የበዓል ዝግጅት

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21 ፣ 2013 የስቅለት እና የትንሳኤ በዓላትን ምክንያት በማድረግ ወቅቱን ያገናዘበ የፀጥታ ዕቅድ አውጥቶ ወደ ተግባር መግባቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡በበዓላት መዳረሻ ወቅቶች ከወትሮው በተለየ ጨምሮ የሚታየውን የሰዎች እና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ተከትሎ የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት እና በተለይም በግብይት፣ በመዝናኛ ሰፍራዎች እና በዕምነት ተቋማት አካባቢ ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ ከወትሮው የተለየ ዝግጅት በማድረግ የፀጥታ ስራ እንደሚያከናውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውሷል፡፡

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ እንደገለፁት የዘንድሮው የስቅለት እና የትንሳኤ በዓላትም ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበሩ እና የግብይት ስፍራዎችን እና የዕምነት ተቋማትን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የወቅቱን የፀጥታ ሁኔታ ያገናዘበ የፀጥታ ዕቅድ በማውጣት እና ለአመራርና አባላቱ ግንዛቤ በማስጨበጥ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡

በተለይም በዓሉን ምክንያት አድርገው የገበያ አለመረጋጋትን ለመፍጠር ምርት በሚደብቁ እና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ለማድረግ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ተናግረዋል፡፡

ለፖሊሳዊ አገልግሎትም ሆነ መረጃ እና ጥቆማ ለመስጠት በነፃ የስልክ መስመር 991 እንዲሁም በ011-1- 11-01-11 መጠቀም እንደሚቻል ያስታወሱት ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ህብረተሰቡ በዓሉን ለማክበር ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ወንጀል የሚፈፅሙ ግለሰቦችም ግርግሩን በመጠቀም ተመሳስለው ስለሚንቀሳቀሱ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚስፈልግ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *