ዩጋንዳ የኮቪድ-19 መከላከያ ያልተከተቡ ሰዎችን በገንዘብና በእስራት መቅጣት የሚያስችል ህግ አረቀቀች::
አዲስ አበበ፣ የካቲት 16፣ 2014 ዩጋንዳ የኮቪድ-19 መከላከያ ያልተከተቡ ሰዎችን በገንዘብና በእስራት መቅጣት የሚያስችል ህግ አረቀቀች፡፡ ለሀገሪቱ ፓርላማ የቀረበው ይህ የህግ ረቂቅ ክትባት ለመውሰድ አሻፈረኝ በሚሉ ዜጎች ላይ 1 ሺህ 139 ዶላር ወይም 4 ሚሊዮን የሀገሪቱን ገንዘብ የሚያስቀጣ ሲሆን የሥድስት ወር እስራትንም ያካትታል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ጄን ሩት አሴንግ ረቂቅ ህጉን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ዜጎችን ከበሽታና ከሞት ለመታደግ ሲባል ህግን በማያከብሩት ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ 45 ሚሊዮን የህዝብ ብዛት ያላት ዩጋንዳ በአንድ ዓመት ውስጥ 16 ሚሊዮኑ ብቻ መከተባቸው የሀገሪቱን መንግስት አሳስቦታል ነው የተባለው፡፡
ከሁለት ዓመት የእንቅስቃሴ እቀባ በኋላ ሁሉም የንግድና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ሙሉ በሙሉ የተከፈቱ ሲሆን በእንቅስቃሴ ወቅት ቫይረሱ እንዳይስፋፋ ክትባት አስገዳጅ እዲሆንም ሀገሪቱ ደንግጋለች፡፡ በዩጋንዳ ቫይረሱ ከተከሰተ ጀምሮ 163 ሺህ ዜጎች በበሽታው የተያዙ ሲሆን ከነዚህም መካከል 3 ሺህ
500 ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል፡፡ እስካሁን በዓለማችን ከ428 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ደግሞ ከ5 ሚሊዮን መሻገሩ ይታወቃል፡፡