ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ቻይና በታይዋን ላይ ጥቃት የምትሰነዝር ከሆነ ሀገራቸው ጣልቃ እደምትገባ አስጠነቀቁ፡፡
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2014 ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ቻይና በታይዋን ላይ ጥቃት የምትሰነዝር ከሆነ ሀገራቸው ጣልቃ እደምትገባ አስጠነቀቁ፡፡ ባይደን በእስያ ጉብኝታቸው ጃፓን ተገኝተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ቤጂንግ በታይዋን ላይ አንዳች ጥቃት ለማድረስ ከሞከረች ሀገራቸው የሃይል እርምጃ እንደምትወስድ ነው የተናገሩት፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ዋሽንግተን ታይዋንን ከቻይና ጥቃት የመጠበቅ ሀላፊነት አለባት ብለዋል፡፡
ከጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ ጋር በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ዙሪያ የተወያዩት ባይደን ቶኪዮና ዋሽንግተን የቻይናን የባህር ሃይል እንቅስቃሴ በቅርበት ይከታተላሉ ብለዋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች ባደረጉት ውይይት በተለይ ሩሲያና ቻይና የሚያርጓቸውን የጋራ ወታደራዊ ልምምዶች በጥንቃቄ እደሚያጤኗቸው መናገራቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ባይደን በመግለጫቸው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬንን ማንነት ለማጥፋት በከፈቱት አረመኔያዊ ጦርነት ዋጋቸውን ይክፍላሉ ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ በወቅታዊው የዩክሬንና ሩሲያ ጉዳይ ለመወያየት በእስያ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ባይደን የቻይናን ዓለም አቀፍ ተፅእኖ መቀነስ የሚያስችሉ ድጋፎችን ለማግኘት ምክክሮችን እያደረጉ መሆናቸውም ተነግሯል፡፡