ሃገሪቱ ውስጥ እየታየ ያለው ለውጥ በኢኮኖሚ እድገት ካልተደገፈ ቀጣይነቱ ያሳስባል ተባለ
አርትስ 29/12/2010
በኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩትና በብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን ትብብር ፤በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኢኮኖሚ ፎረም በአዲስ አበባ ተካሄዷል፡፡
በፎረሙ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ባለፉት አመታት መልካም ስኬቶች መኖራቸውን ጠቅሰው ችግሮች መኖራቸውንም አሳውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 20 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች በድህነት ውስጥ መኖራቸውን እና በ2010ዓ.ም 25 ቢሊዮን የውጭ ብድር መኖሩን እንደማሳያ ጠቅሰዋል፡፡
እየታዩ ላሉት ችግሮች የትኛውም የማህበረሰብ ክፍል የመፍትሄ አካል መሆን እንደሚገባው የጠቆሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከሃገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚዛመዱ ማናቸውንም የፖሊሲም ሆነ የአሰራር ለውጥ እስከማድረግ መንግስት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከኢኮኖሚው ማህበረሰብ ጋር በተደረገው ውይይት በዘርፉ ያልተፈቱ ችግሮች እንዳሉ ማሳያ ነው ያሉት ደሞ የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር እዮብ ተካልኝ ናቸው፡፡ በቀጣይም ጥንቃቄ የተሞላበት አመራር መሰጠት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
በሃገሪቱ እየታዩ ያሉትን ለውጦች እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ፤ ኢኮኖሚ ተኮር ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች ጠቁመዋል፡፡