ሊቨርፑል ወደ ፕሪምየር ሊጉ መሪነት ተመልሷል
የ32ኛው ሳምንት መርሀግብር የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ቅዳሜና እና እሁድ ተካሂደዋል፡፡
የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ትናንት ምሽት ሲደረግ፤ የመርሲ ሳይዱ ሊቨርፑል በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም የለንደኑን ቶተንሃም አስተናግዶ በመጨረሻ ሰዓት በተገኘች ግብ ቀያዮቹ 2 ለ 1 ድል ተቀዳጅተዋል፡፡
ባለሜዳዎቹ በብራዚላዊው ሮቤርቶ ፊርሚኖ የጭንቅላት ኳስ እና አልደርዊልድ በራሱ መረብ ላይ አስቆጥሮ ሊቨርፑል ወደ ሊጉ መሪነት እንዲመለስ፤ ነጭ ለባሾቹ ደግሞ ከምርጥ አራቶች ቡድን ዝርዝር ውስጥ እንዲወጡ ያመቻቸ የጨዋታ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ ሉካስ ሞራ የስፐርሶችን ግብ አስቆጥሯል፡፡
የመርሲ ሳይዱ ቡድን ምስጋና ባለቀ ሰዓት ለተቆጠረችው ግብ ይግባና፤ የፕሪምየር ሊጉን መሪነት በ79 ነጥብ ተረክበዋል፡፡
ቅዳሜ በሳምንቱ መርሀግብር መክፈቻ ግጥሚያ ማንችስተር ሲቲ ወደ ለንደን ተጉዞ ፉልሃምን በሜዳውና ደጋው ፊት 2 ለ 0 በመርታት የነጥብ መጠኑን ወደ 77 ከፍ አድርጓል፡፡
አንድ ቀሪ ጨዋታ ያለው የፔፕ ጓርዲዮላው ሲቲ በርናርዶ ሲልቫ እና ሰርጂዮ ኩን አጉዌሮ ጎሎች የማሸነፊያ ጎሎችን ከመረብ አገናኝተዋል፡፡
የምዕራብ ለንደኑ ቼልሲ ዌልስ ላይ ካርዲፍ ሲቲን ከመመራት ተነስቶ የ2 ለ 1 ውጤት በማስመዝገብ የማውሪዚዮ ሳሪ ልጆች ሶስት ነጥብ አሳክተዋል፡፡
የሴዛር አዝፒሊኮይታ እና ሮበን ሎፍተስ ቺክ ጎሎች ሰማያዊዎቹ ያላቸውን የነጥብ ብዛት ወደ 60 ከፍ በማድረግ ከአርሰናል ጋር ያላቸውን የነጥብ መጠን አስተካክለዋል፡፡ በደረጃ ሰንጠራዡ ግን አሁንም ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
ማንችስተር ዩናይትድ በማርከስ ራሽፈርድ እና አንቶኒ ማርሽያል ጎሎች ታግዘው ኦልድ ትራፎርድ ላይ ዋትፎርድን 2 ለ 1 ሲረታ፤ ቀያይ ሰይጣኖቹ ያላቸውን የነጥብ መጠን ወደ 61 አሳድገው አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡
ከትናንት በስቲያ በተደረጉ ሌሎች ጨዋታዎች፤ በርንሌ ቱርፍሞር ላይ፤ ክሪስታል ፓላስ በሴል ኽረስት ፓርክ ሀደርስፊልድን ፤ ሌስተር ሲቲ በኪንግ ፓወር ቦርንመዝን እና ኢቨርተን በለንደን ስታዲየም ዌስት ሀም ዩናይትድን በተመሳሳይ የ2 ለ 0 ውጤት ድል ሲያደርጉ፤ ሳውዛምፕተን ወደ አሜክስ መጥቶ ብራይተንን 1 ለ 0 አሸንፏል፡፡
የሳምንቱ መርሀግብር መቋጫ ጨዋታ ዛሬ ምሽት ይከናወናል፡፡
በኡናይ ኤመሪ የመራው አርሰናል ኤመሬትስ ላይ የራፋኤል ቤኒቲዙን ኒውካስትል ዩናይትድ ምሽት 4፡00 ያስተናግዳል፡፡
በዛሬ ምሽቱ ጨዋታ መድፈኞቹ ድል የሚቀናቸው ከሆነ የጎረቤቶቻቸውን ቶተንሃም የሶስተኝነት ደረጃ በመቀማት ይደላደላሉ፡፡