መቐለ እና ባህር ዳር ከነማ ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት ደረጃቸውን አሻሽለዋል
መቐለ እና ባህር ዳር ከነማ ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት ደረጃቸውን አሻሽለዋል
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተስተካካይ መርሀግብር ሶስት ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት በክልል ስታዲየሞች ተከናውነዋል፡፡
መቐለ 70 እንደርታ በትግራይ ስታዲየም ፋሲል ከነማን አስተናግዶ 1 ለ 0 በመርታት ወደ ቀድሞው ቦታው ተመልሷል፡፡
ለትግራዩ ቡድን የአሸናፊነት ግቧን አማኑኤል ገብረሚካኤል በሁለተኛው አጋማሽ ማስቆጠር ችሏል፡፡
ይህን ተከትሎ መቐለ በሊጉ የደረጃ ሰንጠራዥ ዕኩል ከጊዮርስ እና ሲዳማ ቡና ጋር 26 ነጥቦችን በመሰብሰብ ከቅዱስ ጊዮርጊስ አንሶ ከሲዳማ በልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተፈናጥጧል፡፡
ባህር ዳር ከነማ ደግሞ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የትግራዩን ስሑል ሽረ አስተናግዶ 2 ለ 0 በመርታት ከተከታታይ የአቻ ውጤት መውጣት ችሏል፡፡
ፍቃዱ ወርቁ እና እንዳለ ደባልቄ ደግሞ ለጣና ሞገዶቹ ቡድን የአሸናፊነት ግቦችን ከመረብ አገናኝተዋል፡፡ ሞገዶቹ በሊጉ በ21 ነጥቦችና አምስት ንፁህ ግቦች ወደ ስድስተኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል፡፡
ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ ጅማ ላይ ከድሬዳዋ ከነማ ጋር ተገናኝተው ሳይሸናነፉ በ3 ለ 3 አቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡ እንግዳው የምስራቁ ቡድን የመሪነቱን ሚና ቢወስድም ለድል ግን ሊበቃ አልቻለም፡፡ ገናናው ረጋሳ፣ ራምኬል ሎክ እና ፍሬድ ሙሸንዲ ለድሬዳዋ ሲያስቆጥሩ፤ ማማዱ ሲዲቤ 2× እና አስቻለው ግርማ ለጅማው ቡድን ከመረብ ማገናኘት ችለዋል፡፡ ስድስቱም ግቦች በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተቆጥረዋል፡፡ ሁለቱም ክለቦች በዕኩል 14 ነጥቦች በግብ መጠን ተበላልጠው 10ኛና 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
ስሑል ሽረ፣ ደቡብ ፖሊስና ደደቢት አሁንም ወራጅ ቀጠናን የሙጢኝ ብለዋል፡፡
በሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን ምንይሉ ወንድሙ ከመከላከያ በ11 ጎሎች ሲመራ፤ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከመቐለ 70 እንደርታ እና አዲስ ግደይ ከሲዳማ ቡና በ9 ጎሎች ይከተላሉ፡፡