መንግስት በምእራብ ኦሮሚያ የኦነግ ወታደሮች ላይ የአየር ጥቃት ፈጸመ ተብሎ የተሰራጨው መረጃ መሰረተ ቢስ ነው ተባለ
መንግስት በምእራብ ኦሮሚያ የኦነግ ወታደሮች ላይ የአየር ጥቃት ፈጸመ ተብሎ የተሰራጨው መረጃ መሰረተ ቢስ ነው ተባለ
በምእራብ ኦሮሚያ በሚገኙ ዞኖች መንግስት የአየር ጥቃት ፈፅሟል በሚል የሚናፈሰው ወሬ ከእውነት የራቀ መሆኑን የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ።
የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሸን ጉዳዮች ቢሮ ባወጣው መግለጫ፥ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ ላይ የሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ህዝቡን ለማደናገር ሙከራዎች እየተደረጉ ነው ብሏል።
የመንግስት ጦር በሰላማዊ ዜጎች ላይ እርምጃ እየወሰደ ነው የሚለው እና የአየር ጥቃት በመፈፀም ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው በሚል የተሰራጨው መረጃም ከእውነት የራቀ መሆኑን ቢሮው አስታውቋል።
በዚህ ዙሪያ ያለው ሀቅ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ስራውን በጥናት ላይ በመመስረት እና ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ እያከናወነ መሆኑ ነው ብሏል። እንደ ኤፍ ቢ ሲ ዘገባ በአካባቢው ላይ ያለው የፀጥታ ችግር ይህን ያክል የአየር ጥቃት እስከመውሰድ የሚያደርስ አይደለም ብሏል ቢሮው ።
መንግስት አሁንም ቢሆን የህዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ያለበትን ሀላፊነት እና ግዴታ ለመወጣት የጀመረውን ስራ ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ የሚያስቀጥል ነው ያለው የክልሉ መንግስት የአካባቢው ህዝብ ወንጀለኞችን አሳልፎ መስጠቱን እንዲቀጥል እና ለሰላም የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አቅርቧል።