ማንችስተር ሲቲ ወደ ዋንጫው እየገሰገሰ ነው
የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የተስተካካይ መርሀግብር ተጠባቂ ጨዋታዎች ትናንት ምሽት ተከናውነዋል፡፡
በጉጉት በተጠበቀው የማችስተር ዩናይትድ እና ማንችስተር ሲቲ የማንቹሩያን ደርቢ ግጥሚያ፤ በሲቲ አሸናፊነት ተጠናቅቋል፡፡
ፈጣን የጨዋታ እንቅስቃሴ እና የመልሶ ማጥቃት የተላበሰው የምሽቱ ጨዋታ በውሃ ሰማያዊዎቹ 2 ለ 0 ድል አድራጊነት ሲጠናቀቅ በርናርዶ ሲልቫ እና ሊሮይ ሳኔ ከመረብ አገናኝተዋል፡፡
ማንችስተር ሲቲ ለሻምፒዮንነት፤ ሌላኛው የከታማ ተቀናቃኙ ክለብ ደግሞ ለደረጃ ሲጫወቱ በሙሉ ግጥሚያው ሁለቱም ቡድኖች አሸናፊ ሁነው ለመውጣት እና ግብ ለማስቆጠር ያደረጉት ትጋት በመጀመሪያው አጋማሽ ጎል ያላስመለከተን ቢሆንም ዘ ሲቲዝንስ ከሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ጅማሮ አንስቶ ወደ ግብ በመድረስ የተሻሉ ነበሩ፤ ያገኟቸውንም አጋጣሚዎች ወደግብነት ቀይረው የሊጉን መሪነት በአንድ ነጥብ ልቀው በ89 ነጥቦች ከሊቨርፑል መረከብ ችለዋል፡፡
ዩናይትድ በ64 ነጥቦች ስድስተኛ ደረጃ ላይ አሁንም ይገኛል፡፡
አርሰናል ወደ ሞሊኒክስ ስታዲየም አምርቶ በኑኖ ስፕሪቶ ሳንቶውቨ ወልቨርሃምፕተን 3 ለ 1 ተሸንፏል፡፡ ሩቢን ኔቬስ፣ ማት ዶኽርቲ እና ዲዬጎ ጆታ የወልቭስን የድል ጎሎች ከመረብ ሲያገናኙ፤ ለመድፈኞቹ በምሽቱ ብቸኛዋን የማስተዛዘኛ ግብ ግሪካዊው ተከላካይ ሶቅራጥስ ፓፓስታቶፖሎስ አስቆጥሯል፡፡
አርሰናል በ66 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ሊጉ ሊጠናቀቅ የሶስት ሳምንታት ዕድሜ የሚቀረው በመሆኑ እና ቡድኖች ያላቸው ነጥብ መቀራረቡ፤ በቀጣይ የሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ የሚመዘገቡ ውጤቶች በተለይ ለሻምፒዮንነት እና የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ የሚደረገው ትንቅንቅ በበለጠ ይጠበቃል፡፡