ማንችስተር ዩናይትድ ከ አርሰናል ተጠባቂ ጨዋታቸውን ዛሬ ምሽት ያደርጋሉ
ማንችስተር ዩናይትድ ከ አርሰናል ተጠባቂ ጨዋታቸውን ዛሬ ምሽት ያደርጋሉ
አርትስ ስፖርት 26/03/2011
በ15ኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ምሽት 5፡00 ላይ በግዙፉ ኦልድ ትራፎርድ ስታዲየም፤ በእንግሊዝ እግር ኳስ ታሪክ ትልቅ የሆነ የታሪክና ባህል ተቀናቃኝነት ጭምር ያላቸው ቡድኖች ማችስተር ዩናይትድ እና አርሰናል መካከል 229ኛ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
ሁለቱ ተቀናቃኞች የመጀመሪያ ግንኙነታቸው በ1894 ሲሆን እስካሁን በተደረጉ የ228 የጨዋታ ግንኙነቶች፤ ቀያይ ሰይጣኖቹ 96፣ መድፈኞቹ 82 ጊዜ አሸናፊ ሲሆኑ በ50 ያህል ግጥሚያዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡
ሰር አሌክስ ፈርጉሰን የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ፤ አርሰን ቪንገር ደግሞ የአርሰናል አለቃ በነበሩበት ጊዜ የሁለቱ ተቀናቃኝነት ጎልቶ ሲታይ፤ በአሁኑ ጊዜ የሰሜን ለንደኑ ክለብ በኡናይ ኢምሪ እየተመራ መልካም ሊባል የሚችል ጉዞን እያደረገ ሲሆን በአንፃሩ የማንችስተር ከተማ ኩራትነቱ በማ.ሲቲ እየተነጠቀ የሚገኘው ዩናይትድ በጆዜ ሞሪንሆ ወጣ ገባ አቋም እያሳየ ዛሬ ምሽት ይገናኛሉ፡፡
በምሽቱ ወቅታዊ አቋማቸውን በማጤን የአሸናፊነቱ ግምት ለአርሰናል ቢሰጥም፤ ሞሪንሆ ታላቅ ጨዋታ ላይ የሚሰጡት ትኩረትና ያላቸው ስኬት፤ ድልን ለእርሳቸው ቡድን ግምት እንዲሰጥ ያደርጋል፡፡
በ15ኛው ሳምንት ትናንት ምሽት የሊጉ መሪ ማንችስተር ሲቲ ዋትፎርድን በሊሮይ ሳኔና ማህሬዝ ግቦች 2 ለ 1 በመርታት ነጥቡን ወደ 41 ከፍ አድርጓል፡፡
ምሽት 4፡ 45 ሲል በርንሊ ከ ሊቨርፑል፣ ኢቨርተን ከ ኒውካስትል ዩናይትድ፣ ፉልሃም ከ ሌስተር ሲቲ፣ ወልቨርሃምፕተን ዋንደረርስ ከ ቼልሲ ይጫወታሉ፡፡