ሱዳናዊያን በመካከላቸው ያለውን አለመግባባት በሰላማዊ ውይይት መፍታት ይበጃቸዋል ሲሉ የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ
ሱዳናዊያን በመካከላቸው ያለውን አለመግባባት በሰላማዊ ውይይት መፍታት ይበጃቸዋል ሲሉ የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ
ምክተል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ጥሪ ያቀረቡት በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ በሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ እየመከረ ባለው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ውይይት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ንግግራቸው የሱዳን ፖለቲከኞችና ባለድርሻ አካላት በመካከላቸው ያለውን አለመግባባት በሰላማዊ ውይይት መፍታት እንደሚገባቸው ነው ምክራቸውን የለገሱት።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በንግግራቸው ኢትዮጵያ በሱዳን አሁን የተከሰተውን አስቸጋሪ ሁኔታ በጥበብ በመፍታት የሱዳንን ሉኣላዊነት እና ነፃነት እንደሚያስጠብቁ በሱዳን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሙሉ እምነት አላት ነው ያሉት።
በዚህም ኢትዮጵያ የሱዳንን ህዝብ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን ገልጸው፣ በሱዳን የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ያለ መግባት መርህን ትከተላለችም ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪም በአፍሪካ ህብረት የተዘጋጀውን የውይይት መድረክ ኢትዮጵያ እንደምትደግፍ ገልጸው፣ ኢትዮጵያ እንደ ኢጋድ ሊቀመንበርነቷና እንደ አፍሪካ ህብረት አባልነቷ ለችግሩ አፍሪካዊ መፍትሄ ለመሻት በሙሉ አቅሟ እንደምትሰራም አስታውቀዋል።
ስብሰባው የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር በሆኑት የግብጹ ፕሬዝዳንት አብደልፈታህ አልሲሲ አማካኝነት የተመራ ሲሆን፤ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማትን ጨምሮ የጅቡቲ፣የኬንያ፣የሶማሊያ፣የሩዋንዳ እና የደቡብ ሱዳን መሪዎች በውይይቱ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል።
በዚሁ ስብሰባ የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳደር እንዲያስረክብ ውሳኔ ተላልፏል።
በተጨማሪም የአፍሪካ ህብረት ከዚህ በፊት ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ የቀረው የአንድ ሳምንት ጊዜ ብቻ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳደር ለማስተላለፍ የሚያስችሉ ስራዎችን ለማጠናቀቅ እንዲችል ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ውሳኔ ተላልፏል።
ከህብረቱ ስብሰባ አስቀድሞ በሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ሊቀመንበር በሆነችው ኢትዮጵያ የተመራው የኢጋድ አባል አገራት መሪዎች ውይይት ተካሂዷል።