loading
ሱዳን ለወራት ለዲፕሎማቶቿ ደሞዝ አልከፈለችም

የዳቦ ዋጋ በሶስት እጥፍ በመጨመሩ ምክንያት ለሳምንታት በህዘባዊ አመፅ እየታመሰች ያለችው ሱዳን የደረሰባት ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በውጭ ሀገራት የሚገኙት ዲፕሎማቶቿ ከሰባት ወራት በላይ  ያለ ደሞዝ እንዲቆዩ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡

ሚድል ኢስት ሞኒተር እንደዘገበው በእስያ እና በአውሮፓ ያሉ የሱዳን አምባሳደሮች ከግማሽ ዓመት በላይ ደሞዛቸው ሳይከፈላቸው ቆይተዋል፡፡

በዚህም የተነሳ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዳርዲሪ ሞሀመድ አህመድ ከፋይናንስ ሚኒስቴር እና ከሀገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ጋር የጋራ ኮሚቴ አቋቁመው ችግሩን ለመፍታት ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ፡፡

እስካሁን ሁኔታውን በአደባባይ ደፍረው የተናገሩት የቀድሞው የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሀመድ ጋንዱር ናቸው ተብሏል፡፡

ሀገሪቱ ያጋጠማት ችግር እንዲህ በቀላሉ ተነግሮ የሚያልቅ እንዳልሆነ የተናገሩት ጋንዱር በውጭ የሚኖሩ ዲፕሎማቶች ደሞዛቸው ብቻ ሳይሆን የህንፃ ኪራይ መክፈል እንዳቃታቸውም አልደበቁም፡፡

የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደሚሉት ያለ ደሞዝ ለወራት የቆዩት ዲፕሎማቶች ወደ ሀገራችን የመመለስ ፍላጎት አላቸው፡፡

ሱዳን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የገጠማት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ገንዘቧ ከዶላር ጋር ያለው ምጣኔ በእጅጉ እንዲወርድ አድርጎታል፡፡

በዚህም ምክንያት የዋጋ ግሽበት በማሻቀቡ ነዋሪዎቿ የዕለት ፍጆታቸውን መግዛት ቢያቅታቸው በመንግስት ላይ ለሳምንታት የዘለቀ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ይገኛሉ፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *