ሱዳን ለፀጥታው ምክር ቤት የህዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር እንዲጀምር የሚያሳስብ ደብዳቤ ላከች::
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 26፣ 2012 ሱዳን ለፀጥታው ምክር ቤት የህዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር እንዲጀምር የሚያሳስብ ደብዳቤ ላከች::
የሱዳን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ተደራዳሪዎቹ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የሶስትዮሽ ውይይቱን በፍጥነት እንዲጀምሩና በተናጠል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ የሚጠይቅ ደብዳቤ ነው የላከው ተብሏል፡፡የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ አሳም ሞሀመድ አብደላ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በላኩት ደብዳቤ በድርድሩ ሂደት የሱዳን አቋም ምን እንደሆነ ማብራሪያ ሰጥተዋል ነው የተባለው፡፡ኢጂፕት ቱዴይ እንደዘገበው ሱዳን ምንጊዜም በመተማመን ላይ የተመሰረተ ድርድር እንዲካሄድ እና የሚደረጉ ውይይቶችም አለም አቀፍ የውሃ አጠቃቀም ህግን መሰረት ያደረጉ እንዲሆኑ ቁርጠኛ አቋም እንዳላት ሚኒስትሯ በደብዳቤያቸው ገልፀዋል፡፡የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ከአሁን ቀደም ከግብፅ እና ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር በጉዳዩ ዙሪያ መምከራቸውን ያስታወሰው ደብዳቤው ሀገራቱ ተቀራርበው እንዲደራደሩ የፀጥታው ምክር ቤት እንዲያግዝ የሚጠይቅ ነው ተብሏል፡፡
ግብፅ የግድቡ የውሃ ሙሌት እንዳይጀመር ደጋግማ ብትጠይቅም ኢትዮጵያ ግን ውሃ የመሙላቱ ሂደት ግድቡ እስኪያልቅ እንጂ ፈቃድ የሚጠብቅ እንዳልሆነ አቋሟን ገልፃለች፡፡