ሱዳን አንዱን እየፈታች ሌላውን ማሰሯን ቀጥላለች፡፡
ሱዳን አንዱን እየፈታች ሌላውን ማሰሯን ቀጥላለች፡፡
ሰሞኑን አሜሪካ ባደረገችባት ጫና ምክንያት ከ2 ሺህ 400 በላይ እስረኞችን የፈታችው ካርቱም አሁን ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራችን ማሰሯ ተሰምቷል፡፡
ፖለቲከኞቹ ለእስር የተዳረጉት ካርቱም ውስጥ አልበሽርን ለማውረድ የሽግግር መንግስት ይመስረት የሚል አቤቱታ ለማቅረብ ዝግጅት ላይ በነበሩበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡
ሚድል ኢስት ሞኒተር እንደዘገበው ከታሳሪዎቹ መካከል የሱዳን ኮሙኒስት ፓርቲ መሪ፣ የኡማ ፓርቲ ምክትል አመራር፣ እንዲሁም የሞያ ማህበራት መሪዎች እና የፓርቲ ፀሀፊዎች ይገኙበታል፡፡
በቦታው የነበሩ የዓይን እማኞች ለጋዜጠኞች ሲናገሩ የተያዙት ሰዎች የፖለቲካ እስረኞች ወደሚጠበቁበት ህንፃ ሲወሰዱ አይተናል ብለዋል፡፡
ከፈረንጆቹ ታህሳስ 19 ጀምሮ በሱዳን የተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመፅ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
መንግስት እስካሁን ሁለት የህግ አስከባሪዎችን ጨምሮ 32 ሰዎች ሞተዋል ቢልም ገለልተኛ ነን የሚሉ አካላት ግን የሟቾቹን ቁጥር ወደ 60 ያስጠጉታል፡፡
መንገሻ ዓለሙ