loading
ሱዳን ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ጋር ለመተባበር መዘጋጀቷን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀማዶክ ተናገሩ::

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2013  ሱዳን ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ጋር ለመተባበር መዘጋጀቷን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀማዶክ ተናገሩ:: ሀምዶክ በሳምንቱ መጨረሻ የአይ.ሲ.ሲ ዋና አቃቤ ህግ የሆኑትን ፋቱ ቤንሱዳን ተቀብለው አነጋግረዋል ነው የተባለው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ሱዳንን የጎበኙት አቃቤ ህጓ በሀገሪቱ በካቢኔ ጉዳዮች እና በፍትህ ሚኒስቴሮች አስተባባሪነት የተዘጋጀውን ስብሰባ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ጋር አካሂደዋል፡፡

የቤንሱዳ ጉብኝት ሁለት ዓላማዎችን ለማሳካት ያለመ ሲሆን አንደኛው በዳርፉር የተፈፀመው የጦር ወንጀል በዓለለም አቀፉ ፍርድ ቤት እንዲዳኝ ሂደቱን ለማመቻቸት፣ ሁለተኛው ደግሞ በተፈላጊዎቹ ዙሪያ መረጃ በጋራ ለማሰባሰብ ነው ተብሏል፡፡ ቤንሱዳ በውይይቱ ወቅት ከሁለት ከፍተኛ ባለ ስልጣኖቻቸው ጋር በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ስለሚፈለጉት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ጉዳይ ለሀምዶክ አንስተውባቸዋል ተብሏል፡፡

ሱዳን ትሪቢዩን እንደዘገበው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍትህ እንዲከበር በቁርጠኝነት የምንሰራው በዋነኝነት አብዮቱ ሲጀመር ይዞት የተነሳውን ዓላማ ለማሳካት ነው በማለት ፕሬዚዳንቱን ኣሳልፈው ለመስጠት ማሰባቸውን የሚያመላክት ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡ አቃቤ ህጓ ከስብሰባው በኋላ በሰጡት መግለጫ ሁሉም የሱዳን ባለ ስልጣናት ከአለም አቀፉ ፍርድ ቤት ጋር እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በዳርፉር በአልበሽር ቀጥተኛ ትእዛዝ ተፈፀመ በተባለው የጦር ወንጀል ከ300 ሺህ በላይ ንፁሀን ዜጎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማረጋገጡን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *