ሶማሊያ በጥቅምት ወር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለማድረግ አቅዳለች ተባለ፡፡
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 23፣ 2013 ሶማሊያ በጥቅምት ወር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለማድረግ አቅዳለች ተባለ፡፡ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ የሶማሊያ የፖለቲካ መሪዎች የዘገየውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጥቅምት 10 ለማካሄድ መስማማታቸውን አስታውቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሃመድ ሁሴን ሮቤል በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ የተካሄደውን የሁለት ቀናት ውይይት ተከትሎ ባለድርሻ አካላት በውክልና የሚካሄደውን የፓርላማ እና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ይፋ አድርገዋል ሲል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
የምክር ቤቱን አመራሮች አደንቃለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተስማሙበት የጊዜ ሰሌዳ እና ሂደቶች ላይ በመመርኮዝ ምርጫው ሰላማዊ እና ግልጽ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ እና የሶማሊያ አምስት ግዛቶች መሪዎች የስልጣን ዘመናቸው የካቲት ወር ከመጠናቀቁ በፊት በድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ መስማማት ባለመቻላቸው ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ የሕገ-መንግስት ቀውስ ማስነሳት ችሏል። የተወካዮች ምክር ቤት የፕሬዚዳንቱን ስልጣን ለሁለት ዓመታት ማራዘሙንና ሲደረግ የነበረው ድርድር አለመሳካቱን ተከትሎ የፖለቲካ ውዝግቡ በሚያዝያ ወር በሞቃዲሾ ጎዳናዎች ላይ ሁከት እና የተኩስ ልውውጥ ማስከተሉም ይታወሳል፡፡