loading
ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉን መሪነት ከኢትየጵያ ቡና ተረከበ

ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉን መሪነት ከኢትየጵያ ቡና ተረከበ

የ13ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሀግብር ጨዋታዎች አራት ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ተካሂደዋል፡፡
ክልል ስታዲየሞች ላይ ቀደም ብለው በተጀመሩ ሶሰት ግጥሚያዎች፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ትግራይ ክልል አቅንቶ መቐለ ላይ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን 1 ለ 0 በመርታት ጣፋጭ ሶስት ነጥብ አሳክቷል፡፡ የፈረሰኞችን ድል ያሳካች ብቸኛ ግብ ከመረብ ያዋሀደው ደግሞ አጥቂው ሳላዲን ሰዒድ ነው፤ ቡድኑም ያለውን የነጥብ ብዛት ወደ 24 ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡
ከሰሜን ረዥም ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጦ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ የተጓዘው መቐለ 70 እንደርታ ሀዋሳ ላይ ደቡብ ፖሊስን በአማኑኤል ገብረሚካኤል እና ያሬድ ከበደ ጎሎች 2 ለ 1 ድል አድርጓል፡፡ ሔኖክ አየለ ለባለሜዳዎቹ ደቡብ ፖሊስ ከመሸነፍ ያላዳነች ግብ አስቆጥሯል፡፡
ጎንደር ላይ ደግሞ ፋሲል ከነማ እና አዳማ ከተማ ያለግብ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡
አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ጅማ አባ ጅፋርን ያስተናገደው የዲዲዬ ጎሜስ ቡድን ኢትዮጵያ ቡና በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ በተመሳሳይ የ1 ለ 0 ውጤት ከጨዋታ ብልጫ ጋር ተሸንፏል፡፡ ለጅማው ቡድን የአሸናፊነት ግቧን የቀድሞ የቡና ተጫዋች አስቻለው ግርማ ከመረብ አገናኝቷል፡፡
ቡናማዎቹ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ሽንፈት ማስተናገዳቸውን ተከትሎ የሊጉን መሪነት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ማስረከብ ችለዋል፡፡
የሳምንቱ መርሀግብር ቀጣይ ግጥሚያዎች ነገ ሲቀጥሉ፤ ባህር ዳር ከነማ ወደ ወላይታ አምርቶ ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻን 9፡00 ሲል የሚገጥም ይሆናል፡፡ በተመሳሳይ ሰዓት በትግራይ ደርቢ መቐለ ላይ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙት ደደቢት እና ስሑል ሽረ ይጫወታሉ፤ በአዲስ አበባ ስታዲየም ደግሞ መከላከያ ከሀዋሳ በ11፡00 ይፋለማሉ፡፡
ሊጉን ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ተስተካካይ ግጥሚያ እየቀረው በ24 ነጥቦች መምራት ጀምሯል፡፡ ቡና በሁለት ነጥብ አንሶ በ22 ሲከተል፤ ሀዋሳ ከነማ፣ መቐለ 70 እንደርታ፣ ሲዳማ ቡና እና ፋሲል ከነማ በእኩል 20 ነጥቦች በግብ ክፍያ ተበላልጠው ከሶስት እስከ ስድስት ያለውን ደረጃ ተቆናጥጠዋል፡፡
ስሑል ሽረ፣ ደቡብ ፖሊስና ደደቢት አሁንም ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ቡድኖች ናቸው፡፡
ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን ዳዋ ሆቴሳ ከአዳማ እና አዲስ ግደይ ከሲዳማ በ8 ጎሎች ሲመሩ የሀዋሳው ታፈሰ ሰለሞን በ7 ጎል ይከተላል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *