loading
በህገወጥ መንገድ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ በማስገጠም  ሲጠቀሙ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 7፣2013 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የማያውቀውን የኤሌክትሪክ ቆጣሪ በማስገጠም የኤሌክትሪክ ሃይል ሲጠቀሙ የነበሩ ግለሰቦች እና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለፀ። የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ጎሮ ሰፈራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መሆኑ ተመላክቷል። በአካባቢው የሚኖሩ አምስት ግለሰቦች የኤሌክትሪክ ቆጣሪ ለማስገባት ፈልገው ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ  አገልግሎት ምስራቅ ዲስትሪክት አመልክተው ተራ በመጠበቅ ላይ እንደነበሩ የሚገልፅ መረጃ መገኘቱን የመዲናዋ ፖሊስ ጠቅሷል፡፡

ይሁን እንጂ ጉዳዩን እኛ ያለወረፋ እናስፈፅምላችኋለን ብለው ነዋሪዎቹን የቀረቡ ደላሎች ከባለሙያ ጋር አገናኝተው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ  አገልግሎት ዕውቅና ውጪ 5 የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎች  እንዲገጠሙ በማድረግ በሃሰተኛ ደረሰኝ 78ሺህ 450 እንዲከፍሉ አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለአንድ ወር ከቀናት ያህል የሀይል ተጠቃሚ ሆነው ቢቆዩም ቆጣሪው የቴክኒክ ችግር ስለነበረው ተጠቃሚዎቹ ይህንኑ ለተቋሙ ቅሬታ ማቅረባቸውን እና የተቋሙ ባለሙያ ቦታው ድረስ
በመሄድ ሲያረጋግጥ እንዳያገለግሉ የተወገዱ ቆጣሪዎች መሆናቸው መረጋገጡን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅሷል፡፡

ፖሊስ ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ የቀረበለትን አቤቱታ ተቀብሎ ባከናወነው ተግባር  በወንጀሉ ላይ ተሳትፎ አላቸው የተባሉ የተቋሙ ሰራተኞች ፣ደላሎች እና በህገወጥ መልኩ የሀይል ተጠቃሚ የነበሩት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል። ስነ ምግባር የጎደላቸው የተቋሙ ሰራተኞች የሚፈፅሟቸውን ወንጀሎች ጨምሮ በ2013 ዓ.ም ብቻ ከ18 ሚሊየን ብር በላይ ኪሳራ መድረሱን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *