loading
በሊባኖስ የሚኖሩ 450 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ለመመለስ ፈቃድ አገኙ::

አዲስ አበባ፣ነሐሴ 12፣ 2012 በሊባኖስ የሚኖሩ 450 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ለመመለስ ፈቃድ አገኙ:: በቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ቆንላ ጀነራል ተመስገን ዑመር ጽሕፈት ቤቱ በሊባኖስ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን ዜጎች መረጃዎች ለአገሪቱ ኢምግሬሽን ጉዳዮች መሥሪያ ቤት አስገብቶ እንደነበር ለኢዜአ ገልጸዋል። በዚሁ መሠረት የኢሚግሬሽን ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስፈላጊውን ማጣራት ካደረገ በኋላ 450 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ፈቃድ መስጠቱን ተናግረዋል።

ከተመላሾቹ ኢትዮጵያውያን በቤይሩት የወደብ ፍንዳታ ምክንያት በመጠለያ ውስጥ ያሉ እንደሚገኙበትም አመልክተዋል። ቆንስላ ጽህፈት ቤቱ ወደ አገራቸው የሚመለሱ ዜጎችን ዝርዘር በቀጣይ ቀናቶች ውስጥ እንደሚያሳውቅ ጠቁመው፤ የሚመለሱት ዜጎች የትራንስፖርት ወጪያቸውን በራሳቸው የሚሸፍኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ”በስምንተኛው ዙር የሥም ዝርዝራቸውና መረጃቸው ተልኮ ፈቃድ ያላገኙ ኢትዮጵያውን አሉ” ብለዋል አቶ ተመስገን።

በሊባኖስ ሕግ ወንጀል የሰሩ፣ የፍርድ ቤት ጉዳይ ያለባቸው፣ ከአሰሪዎቻቸው ጋር ውል ያልጨረሱና በሌሎች ምክንያቶች ዜጎች የመመለሻ ፈቃድ እንደማያገኙ ገልጸዋል። ይሁንና በሊባኖስ አሁን ካለው አሳሳቢ ሁኔታ አንጻር በልዩ ሁኔታ ኢትዮጵያውያኑ ፈቃድ አግኝተው እንዲመለሱ ለኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤቱ ጥያቄ እንደሚቀርብ አመልክተዋል። ዜጎቹ ለመመለስ ፈቃድ ቢያገኙም የመውጫ ቪዛ ለማግኘት ከሁለት እስከ ሦስት ወር እንደሚፈጅ ተናግረው፤ በፍጥነት ኢትዮጵያውያኑ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አመልክተዋል። ጉዳዩ ከቆንስላ ጽሕፈት ቤቱ አቅም በላይ የሚሆን ከሆነ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ጥያቄ እንዲቀርብ ሊደረግ እንደሚችል ነው አቶ ተመስገን ያስረዱት።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *