loading
በመጪው የትምህርት ዘመን ገቢራዊ የሚደረገው አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ይፋ ሆነ፡፡

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 25፣2013 በመጪው የትምህርት ዘመን ገቢራዊ የሚደረገው አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ይፋ ሆነ፡፡ ከ26 ዓመታት በፊት ጀምሮ በየአምስት ዓመቱ የስርዓተ ትምህርት ክለሳ የሚደረግ ሲሆን ለስድስተኛ ጊዜ የተዘጋጀው የአጠቃላይ ትምህርት ፍኖተ ካርታም ከ2014 ጀምሮ ለአምስት ዓመታት ይተገበራል። ነባሩ ስርዓተ ትምህርት የጥራትና አግባብነት እንዲሁም የሰው ሀብት ሰብዕና ግንባታ ጉድለቶች እንደነበሩት በጉባኤው ላይ ተነስቷል፡፡

ከቅድመ አንደኛ ደረጃ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርትን ያጠቃለለው የአጠቃላይ ትምህርት ፍኖተ ካርታ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ያስችላሉ የተባሉ ዘርፈ በዙ ማሻሻያዎችን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል። በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ግብረ ገብነት፣ አገር በቀል እውቀት፣ ሙያና የቀለም ትምህርት፣ ቴክኖሎጂ፣ ምርትና ተግባር፣ ጥናትና ምርምር ትኩረት የተደረገባቸው ጉዳዮች መሆናቸውም ተጠቅሷል። ቅደመ አንደኛ ደረጃ፣ አንደኛ ደረጃ፣ መካከለኛ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ በሚል እርከን የተከፋፈለው ስርዓተ ትምህርቱ ዘጠኝ የትምህርት መስኮች ይኖሩታል።

እነርሱም ቋንቋ፣ ሂሳብ፣ ተፈጥሮ ሳይንስ፣ ማህበራዊ ሳይንስ፣ ስነ ጥበብ፣ ግብረ ገብነትና የዜግነት አገልገሎት፣ ጤናና ሰውነት ማጎልመሻ፣ ኢንፎርሜሸን ቴክኖሎጂ፣ ስራና ቴክኒክ ትምህርቶች ናቸው። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እርከን አዳዲስ የትምህርት ክፍሎች የተካተቱ ሲሆን ለአብነትም በ12ኛ ክፍል
መልቀቂያ ትምህርቶች ውስጥ ግብርና አንዱ መሆኑ ተገልጿል። የልዩ ፍላጎት፣ የወጣቶችና ጎልማሶች ብርሃን መደበኛ ያልሆነ ትምህርትም በፍኖተ ካርታው ትኩረት ከተሰጣቸው መስኮች መካል ይገኛሉ፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር ከስድስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ከክልል ትምህርት ቢሮዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።  የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ እንዳሉት ባለፉት ሶስት ዓመታት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የለውጥ ስራዎች በትምህርት ዘርፉ እየተተገበሩ ነው። በዚህም አዲሱን ስርዓት ትምህርት 21ኛው ክፍለ ዘመን በደረሰበት መልኩ በቴክኖሎጂ ተደግፎ ገቢራዊ
ይደረጋል ብለዋል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *