በሙስና ወንጀል የሚፈለጉ ግለሰብን ሰነድ አሽሽተዋል የተባሉ ተጠርጣሪ ፍርድ ቤት ቀረቡ
በሙስና ወንጀል የሚፈለጉ ግለሰብን ሰነድ አሽሽተዋል የተባሉ ተጠርጣሪ ፍርድ ቤት ቀረቡ
አርትስ 14/03/2011
በከባድ የሙስና ወንጀል ይፈለጉ የነበሩ የሜቴክ ከፍተኛ የስራ ኃላፊ ብርጋዴር ጄነራል ሀድጉን ሰነዶች እንዲሸሹ አስደርገዋል በሚል ወንጀል የተጠረጠሩት የሜቴክ የሰው ኃይል ልማት ኃላፊ የነበሩት ሌተናል ኮሎኔል ሰጠኝ ካህሳይ ላይ ፖሊስ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ጠየቀ፡፡
ተጠርጣሪው ብርጋዴር ጄነራል ሀድጉ በሙስና ወንጀል እንደሚፈለጉ እያወቁ የተፈላጊው ጸሐፊም ከስራ ሰዓት ውጪ በቅዳሜ ዕለት ቢሮ ገብታ ሰነድ እንድታሸሽ በማድረጋቸው የሙስናን ወንጀል ምርመራን በማደናቀፍ ወንጀል ነው የተጠረጠሩት፡፡
ተጠርጣሪው ቀደም ባለው ጊዜ አቅም ስለሌለኝ መንግስት ተከላካይ ጠበቃ ይመደብልኝ በማለት ያገኙትን ይሁንታ ተከትሎ ፖሊስ ከቀጠሮው በፊት በነበሩት ጥቂት ቀናት ተጠርጣሪው ሃብት እንዳላቸው አጣርቻለሁ ብሏል፡፡
ተጠርጣሪው በ5 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች 250 ሺህ ብር ተቀማጭ እንዳላቸዉ የገለፀው ፖሊስ አቅም እያላቸው የለኝም በማለት ፍርድ ቤቱን አሳስተዋል ብሏል፡፡
ተጠርጣሪው በበኩላቸው ሂሳቦቹ የታገዱ ናቸው፤ ችሎቱም የባንክ ሂሳቦቹን ይመርምርልኝ፤ ከዚህ አንጻር በመንግስት ጠበቃ የመወከል መብቴን ላጣ አይገባም ብለዋል።
ኢቢሲ እንደዘገበዉ ችሎቱም አሁን ያለው ሂሳባቸው ተጣርቶ እንዲቀርብና ተጨማሪ ማስረጃ ፖሊስ ሰብስቦ በሰባት ቀን አንዲያቀርብ በማዘዝ ለህዳር 20 ቀን 2011 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።