loading
በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ 36 የቀድሞ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ተያዙ

አርትስ 03/ 03/2011

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቢህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ማምሻውን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ላለፉት አምስት ወራት በተሰበሰቡ ማስረጃዎችና መረጃዎች መነሻ ነው።

በዚህም በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ውስጥ በተለያዩ የስራ ሃላፊነትና ሙያ ላይ የነበሩ 36 ግለሰቦች ስልጣናቸውን በመጠቀም በፈጸሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች ተይዘዋል።

ግለሰቦቹ ፈጽመዋል ተብለው ከተጠረጠሩባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች ውስጥ በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦችን ማሰቃየት፣ያለህግ አካላት እውቅና በድብቅ ስፍራዎች ማሰር፣ ለስነልቡና ሁከት መዳረግ እና የተጠርጣሪ ቤተሰቦችን ማሰቃየትና ንብረታቸውን መውሰድ  ጥቂቶቹ ናቸው።

የታሰሩ ሰዎችን ጫካ ወስጥ ወስዶ መጣል፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን በማስፈራራት ከፓርቲ እንዲለቁ ማድረግ፣ ከአውሬ ጋር ማሰር፣ ሰዎችን አድራሻቸውን ማጥፋት እና በአካላቸው ላይ ዘግናኝ ጥቃት መፈጸም በተጠርጣሪዎቹ ተፈጽመዋል ከተባሉ ዋና ዋና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ውስጥ ተካትተዋል።

በአዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ተቋሙ ያደራጃቸው ሰባት ስውር እስር ቤቶች እንደነበሩ በመግለጫው ተነግሯል። በነዚህ እስር ቤቶች ለህገወጥ ተግባር ጥቅም ላይ ይውሉ እንደነበርም ተረጋግጧል ተብሏል።

እነዚህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ላይ ከሰፈሩ መርሆች በተቃራኒ የተተገበሩና በየትኛውም ሃገር ይቅርታ የማያሰጡ ወንጀሎች መሆናቸውም ተነግሯል።

የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ በተቋም ደረጃ አሰራር ተደርጎ የተያዘና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት የቀድሞ ሃላፊ በሚሰጡት አቅጣጫ መሰረት የሚፈጸም እንደነበርም በመግለጫው ላይ ተብራርቷል።

ጠቅላይ ዐቃቢ ህጉ አቶ ብርሃኑ እንዳሉት በተለይ ሰኔ 16 ቀን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመግደል የተፈጸመው የቦምብ ጥቃት የተቀነባበረው በዚሁ ተቋም ዋና ሃላፊ አቀናባሪነት ነው ።

 

በዚህም በወንጀሉ የተካፈሉ ናቸው የተባሉት በሙሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ያልተያዙ ቀሪ ግለሰቦች መኖራቸውም ተነግሯል።

በአጠቃላይ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል ተጠርጥረው ከተያዙት 36 ግለሰቦች በተጨማሪ ሌሎችን በወንጀሉ ተካፋይ የነበሩ ቀሪ ግለሰቦችን ለመያዝ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ተብሏል።

ግለሰቦቹ በሃገር ውስጥና ከሃገር ውጪ መደበቃቸው ተጠቁሞ ካሉበት ለመያዝ ህብረተሰቡ ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ ቀርቧል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *