loading
በሰኔ 16 የቦምብ ፍንዳታ ከተጠረጠሩት ግለሰቦች መካከል በአምስቱ ላይ ክስ ሊመሰረት ነው::

ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ድጋፍ ለመስጠት ሰኔ 16 ቀን 2010 በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተዘጋጀ ሰልፍ ላይ ቦምብ በማፈንዳት ከተጠረጠሩ ግለሰቦች መካከል በአምስቱ ላይ ክስ ሊመሰረት ነው።
መርማሪ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ የምርመራ መዝገቡን ለአቃቤ ህግ ያሰረከበባቸው ተጠርጣሪዎች አብዲሳ ቀነኔ፣ ደሳለኝ ተስፋዬ፣ ጌቱ ግርማ፣ ህይወት ገዳ እና ባህሩ ቶላ ናቸው።
የፌደራል ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት አቃቤ ህግ ብርሃኑ ወንድምአገኘሁና አቃቤ ህግ ካሳሁን አውራሪስ የተጠርጣሪዎቹ ጉዳይ እየታየበት ያለበትን የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 1ኛ የወንጀል ችሎት የተረከቡትን የምርመራ መዝገብ የድምፅ ቅጂ፣ የምስልና ዝርዝር ጉዳዮች ምርመራ የያዘ በመሆኑ፥ ክስ መመስረቻ 15 ቀን ይሰጠን ሲሉ ጠይቀዋል።
ተጠጣሪዎች በበኩላቸው ምርመራው ከተጠናቀቀ ለአቃቤ ህግ ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጠው አይግባም፤ የዋስትና መብታችን ይጠበቅ፤ በማረፊያ ቤት የሚያጋጥመንም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይቁም ሲሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ የሰጠው አቃቤ ህግ በበኩሉ የሁለት ዜጎች ህይወት ያለፈበት እና በበርካቶች ላይ ቀላል እና ከባድ ጉዳት የደረሰበት እንዲሁም ድርጊቱ ተቀነባብሮ የተፈፀመ በመሆኑ በምስክሮች ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ስለሚችሉ ዋስትና ሊፈቀድ አይገባም ሲል ተቃውሟል።
ሰብዓዊ መብታቸውን በተመለከተ ምላሽ የሰጠው መርማሪ ፖሊስ፥ በየቀኑ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንደሚገናኙና ባረፉበት አካባቢ ያለውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በየቀኑ የሚያሳይ የቪዲዮ ማስረጃ ስላለ ይህንን የቪዲዮ ማስረጃ ማቅረብ እንችላለን ብሏል።
ድርጊታቸው የተቋም ስምን ማጥፋት ነው፤ ካልሆነ ግን ጉዳዮን የሚከታተል ገለልተኛ አካል ሊመደብ ይችላል ሲል ለፍርድ ቤቱ ምላሽ ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ ሁለቱንም ወገን ካደመጠ በኋላ አቃቤ ህግ የጠየቀውን የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ሰርዓት አንቀፅ 109 ንፁስ ቁጥር 1 መሰረት ክስ መመስረቻ የ15 ቀን ጊዜ ፈቅዳል።
ተጠርጣሪዎችም በማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ያዘዘ ሲሆን፥ ሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ ግን የሚመለከተው ኃላፊ በቀጣይ ቀጠሮ ቀርቦ እንዲያስረዳ አዟል።
የአቃቤ ህግ ክስን ለማየት ለነሃሴ 16 ቀን 2010 ዓመተ ምህረት ቀጠሮ ይዟል።
ቀሪ ተጠርጣሪ የሆኑት የብሄራዊ መረጃ ደህንነት መምሪያ አዛዝ ተስፋዬ ኡርጌን ጨምሮ ሶስት ተጠርጣሪዎች የምርመራ መዝገብ ጉዳይ የፊታችን ረቡዕ በችሎቱ የሚቀርብ ሲሆን፥ የስራ ክፍተት በመፍጠር የተጠረጠሩት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የነበሩት ግርማ ካሳን ጨምሮ ዘጠኝ የፌደራል ፖሊስ አባላትን በተመለከተ ለመጨረሻ ጊዜ የተሰጠው ቀጠሮ ዛሬ ከሰዓት በኋላ የሚታይ ይሆናል። ፋና እንደዘገበዉ፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *