loading
በሴቶች የዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ እንግሊዝ ከአሜሪካ የሚያደርጉት የዛሬ ምሽት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡

ለስምንተኛ ጊዜ በአውሮፓዊቷ ፈረንሳይ እየተሰናዳ የሚገኘው የፊፋ ሴቶች ዓለም ዋንጫ ውድድር የግማሽ ፍፃሜ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

ዛሬ ምሽት 4፡00 ሰዓት ላይ ለዋንጫ ለማለፍ የሚደረገው አንደኛው ጨዋታ በግሮፓማ ስታዲየም በእንግሊዝ እና አሜሪካ መካከል ይከናወናል፡፡

ሁለቱም ብሔራዊ ቡድኖች ለዋንጫው የታጩ ቢሆንም አንዳቸው ጉዟቸው እዚህ ላይ ሊገታ ግድ ይላል፤ ሁለቱም ቡድኖች ከምድብ ጀምሮ በጥሎ ማለፍ እና ሩብ ፍፃሜ ጉዞዎች በመቶ ፐርሰንት ድል እዚህ ደረጃ ደርሰዋል፡፡

በቀድሞው የወንዶች ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ፊል ኔቭል የሚመሩት ሶስቱ አናብስታት በምሽቱ ድል የሚቀናቸው ከሆነ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ድሉ ከ1966 በኋላ እንደ ዋና ቡድን በትልቅ ውድደሮች ፍፃሜ ላይ በመድረስ በታሪክ መዝገብ የሚሰፍር ይሆናል፡፡

ኔቭል ከቢቢሲ ስፖርት ጋር በነበረው ቆይታ ቡድኑ ለጨዋታው ዝግጅቱን እንዳደረገ እና በምን አይነት መንገድ መጫወት እንዳለባቸው እንደሚያውቁ ተናግሯል፡፡  

የሶስት ጊዜ የዓለም ዋንጫውን በማንሳት ትልቅ ታሪክ ያላቸው አሜሪካውያኑ አራተኛ ዋንጫቸውን ወደ ዋሽንግተን ለመውሰድ እያለሙ በምሽቱ ይጫወታሉ፤ ብዙዎቹ የእንግሊዝ እና አሜሪካን ግጥሚያ ከፍፃሜ በፊት የሚደረግ የፍፃሜ ጨዋታ ብለውታል፡፡

ለወርቃማ ጫማው በአምስት ጎሎች እየተፎካከሩ የሚገኙት አሜሪካዊቷ የክንፍ መስመር እና ምክትል አምበል ሜጋን ራፒኖ እና እንግሊዛዊቷ ሉሲ ብሮንዝ የሚያደርጉት ትንቅንቅ ይጠበቃል፡፡

በሩብ ፍፃሜው አሜሪካ የውድደሩን አዘጋጅ ፈረንሳይ 2 ለ 1 እንዲሁም እንግሊዝ ኖርዌይን በ3 ለ 0 ውጤት በመርታት ነው እዚህ ደረጃ የበቁት፡፡    

በሌላኛው የግማሽ ፍፃሜ ግጥሚያ ደግሞ ነገ ምሽት ኔዘርላንድስ እና ስዊድን ይጫወታሉ፡፡        

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *