በሶማሊያ በተፈፀሙ ሁለት የሽብር ጥቃቶች የ48 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተሰማ፡፡
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2014 በሶማሊያ በተፈፀሙ ሁለት የሽብር ጥቃቶች የ48 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተሰማ፡፡ በማዕከላዊ ሶማሊያ በተፈፀሙት ጥቃቶች የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 48 ከፍ ያለ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን የሂርሻቤል ግዛት አስተዳዳሪ የአልሸባብ አማፂያን ከምርጫው በፊት ፖለቲከኞች ላይ ማነጣጠራቸውን
አስታውቀዋል።
መጀመርያ በሂርሻቤል ቤልደዌን አውራጃ በተፈፀመው የአጥፍቶ ጠፊዎች ጥቃት አሚና መሀመድ አብዲን ጨምሮ ሁለት የአካባቢው ህግ አውጪዎች ለዳግም ምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት ከበርካታ ጠባቂዎቻቸው ጋር የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል። ከደቂቃዎች በኋላ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ለህክምና ሲወሰዱበት ከነበረው የቤለድዌን ሆስፒታል ውጭ በመኪና ላይ የተጠመደ ቦምብ ፈንድቶ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ ህንፃዎች ወድመዋል፣ መኪናዎች ተቃጥለዋል።
ኤ.ኤፍ.ፒ. ይሄንን ዜና እስካጠናቀረበት ሰዓት ድረስ በመንትዮቹ የቦምብ ፍንዳታዎች 48 ሰዎች ሲገደሉ 108 ሰዎች ቆስለዋል ያሉት የሂርሻቤል ክልል አስተዳዳሪ የድንገተኛ አደጋ ሰራተኞች በፍርስራሾቹ የተቀበረ አስከሬን ማግኘታቸውን ተናግረዋል። አስተዳዳሪው ዜጎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያሳሰቡ ሲሆን ሁሉም የደህንነት አካላት የፀጥታ ጥበቃውን እንዲያጠናክሩ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡
እነዚህ ጥቃቶች በተፈፀሙበት ዕለት በሞቃዲሾ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ በተፈፀመ ሌላ ጥቃት ሶስት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ሃላፊነቱን በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሰው የሽብር ቡድን አል-ሸባብ ወስዷል። ከአል-ቃይዳ ጋር ግንኙነት ያላቸው እነዚህ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ የሚፈፅሟቸው ጥቃቶች በሶማሊያ ዋና ከተማ እና በሌሎች ከተሞች የሲቪል፣ ወታደራዊና የመንግስት አካላት ላይ ያነጣጠሩ ናቸው።