loading
በታላቁ ቤተ-መንግሥት የዕራት መርሐ-ግብር ከ800 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ፡፡

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2014 በታላቁ ቤተ-መንግሥት የዕራት መርሐ-ግብር ከ800 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ፡፡ በታላቁ ቤተ-መንግሥት በተካሄደው የዕራት መርሐ-ግብር ከትኬት ሽያጭ በቀጥታ ከ800 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ። በመርሐ-ግብሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዳያስፖራ አደረጃጀት መሪዎች፣ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ተገኝተዋል።


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመርሐ-ግብሩ ላይ ባስትላለፉት መልዕክት ዳያስፖራው በአስቸጋሪ ጊዜያት ከሀገሩ ጎን በመቆም ላሳየው አጋርነት እና አለኝታ ምስጋና አቅርበዋል። ዳያስፖራው ለሀገራዊ ጥሪው የሰጠው ምላሽ ምስጋና እና አክብሮት የሚገባው መሆኑን አንስተው፣ ይህ ጅምር ተጠናክሮ ከቀጠለ ሁለተኛ ትውልድ ዳያስፖራዎችን ከሀገራቸው ጋር ለማገናኘት ትልቅ ድልድይ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።


የእስራኤል እና የሌሎች ሀገራት ዳያስፖራዎች ለሀገራቸው ዕድገት ያበረከቱትን አስተዋፅኦ አስታውሰው፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራም በሀገሩ ብልጽግና ውስጥ ከፍተኛ ሚና ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል። ዳያስፖራው ባለበት ሀገር እንዲደመጥ እና በሀገሩ ላይም ያለው ሚና እንዲያድግ መደራጀት ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነም አስገንዝበዋል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትርና የአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራዎች አቀባበል ብሔራዊ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ መርሐ- ግብሩን ስፖንሰር ያደረጉ የዳያስፖራ አደረጃጀቶችን አመስግነዋል።


የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብሩን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ጋር በመተባባር ያዘጋጁትና በአሜሪካና ካናዳ በሚኖሩ ኢትዮጵያውናንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተቋቋሙት የኢክናስ፣ ጌትፋክት፣ ግሊንና ኤፓክ ተወካዮችም በበኩላቸው የኢትዮጵያን መብትና ጥቅም ለማስከበር እያከናወኗቸው ስላሉ ተግባራት ማብራሪያ አቅርበዋል። ድርጅቶቹ እስካሁን ባለው ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ላይ እየተነዙ ያሉ ፕሮፓጋንዳዎችንና የተሳሳቱ ትርክቶችን እንዲሁም ያልተገቡ ጫናዎችን ለመመከት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆናቸውንና ለሀገራዊ ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ ጥሪዎችም ከፍተኛ ሀብት ማሰባሰባቸውን ኤጀንሲው አስታውቋል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *