በትግራይ ጉዳይ የፀጥታው ምክር ቤት መግለጫ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2013 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በትግራይ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ አሳስቦኛል አለ፡፡ምክር ቤቱ ሁኔታውን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ በተለይ በሴቶች ላይ ተፈጸመ የተባለው የመደፈር ጥቃት በእጅጉ አሳሳቢ ነው ብሏል፡፡ በክልሉ በተፈጠረው ግጭት ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ሁኔታዎች አስቸጋሪ ናቸው ያለው ምክር ቤቱ ሁኔታው በፍጥነት መስተካከል አለበት ሲል አሳስቧል፡፡
ኢትዮጵያ በክልሉ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፎች በወቅቱ እንዲደርሱ የምታደርገውን ጥረት እውቅና እንደሚሰጥ የገለጸው ምር ቤቱ አሁንም ግን ሰፊ ስራዎች ይቀራሉ ብሏል የሚደረገጉት ሰብዓዊ ድጋፎች የተረባበሩት መንግስታት ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ መርሆችን በሚመጥን መልኩ እንዲቀጥሉም አሳስቧል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጋራ ሆነው ጉዳዩን እንዲያጣሩ የተነሳውን ሀሳብም ምክር ቤቱ ተቀብሎታል፡፡ የምክር ቤት አባላቱ በሂደቱ ውስጥ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ መብትና ፖለቲካዊ ነፃነቷን ለማክበር ቁርጠኛ አቋም እንዳለው ገልጸዋል፡፡