በቻምፒዮንስ ሊግ አያክስ እና ቶተንሃም ወደ ሩብ ፍፃሜ አልፈዋል
በቻምፒዮንስ ሊግ አያክስ እና ቶተንሃም ወደ ሩብ ፍፃሜ አልፈዋል
የ2018/19 የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የመጨረሻ 16ቱ ቡድኖች ወደ ሩብ ፍፃሜው ዙር ለመቀላቀቀል የመልስ ጨዋታቸውን እያደረጉ ነው፡፡
ትናንት ምሽት ሁለት ግጥሚያዎች ሲከናወኑ፤ አስገራሚ ውጤቶች ተመዝግብዋል፡፡
በስፔን መዲና ማድሪድ ሳንቲያጎ ቤርናቤው ላይ የኔዘርላንዱን አያክስ ያስተናገደው ሪያል ማድሪድ የ4 ለ 1 አሰቃቂ ሽንፈት ገጥሞታል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች ከሁለት ሳምንት በፊት አምስተርዳም ላይ በማድሪድ አሸናፊነት ቢጠናቀቅም፤ በድምር ውጤት አያክስ 5 ለ 3 አሸንፎ ሩብ ፍፃሜውን የተቀላቀለ ቀዳሚ ክለብ ሁኗል፡፡
ለአያክስ ምሽቱን በደስታ ያስፈነጠዙ ጎሎች ሀኪም ዚያች፣ ዳቪድ ኔሬስ፣ ዱሳን ታዲች እና ላዜ ሾኔ ከመረብ አገናኝተዋል፡፡ የማድሪድን ብቸኛ ግብ ማርኮ አሴንሲዮ አስቆጥሯል፡፡
ሌላኛው በተመሳሳይ ሰዓት የተደረገው ጨዋታ ደግሞ ጀርመን ላይ ሲሆን ቦርሲያ በዶርትሙንድ ሴግናል ኤዱና ፓርክ ቶተንሃምን ገጥሞ የ1 ለ 0 ሽንፈት ገጥሞት ከውድድሩ ተሰናብቷል፡፡
ሀሪ ኬን የስፐርሶችን የአሸናፊነት ጎል ከመረብ ያገናኘ ሲሆን ቡድኑ በአጠቃላይ የ4 ለ 0 ድል በማስመዝገብ ከ2011 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሩብ ፍፃሜውን መቀላቀል ችሏል፡፡
ዛሬ ምሽት ሌሎች የመልስ ጨዋታዎች ሲደረጉ ማንችስተር ዩናይትድ ከ ፒ.ኤስ.ጂ እንዲሁም ፖርቶ ከ ሮማ ይካሄዳሉ፡፡