በናይጀሪያ የቦኩሀራም ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት 81 ሰዎች ተገደሉ::
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2012 በናይጀሪያ የቦኩሀራም ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት 81 ሰዎች ተገደሉ:: ታጣቂዎቹ ሞንጉኖ እና ንጋንዛይ በተባሉት የሀገሪቱ አካባቢዎች ላውንቸር እና ሮኬቶችን ጭምር ታጥቀው ከባድ ጥቃት ማድረሳቸውን የአካባው ነዋሪዎች እና የእርዳታ ሰራተኞች ተናግረዋል፡፡ በጥቃቱ 20 የሚሆኑ የመንግስት ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን በስፍራው የነበሩ ቀሪዎቹ ወታሮችም ተዋጊዎችን መመከት አቅቷቸው ሲሸሹ ታይተዋል ነው የተባለው፡፡
የመንግስት ወታደሮችን ጨምሮ ከሞቱት 81 ሰዎች በተጨማሪ በርካታ ሰዎች በጥቃቱ መቁሰላቸውን አልጀዚራ በዘገባው አስነብቧል፡፡
ታጣቂቂዎቹ ጥቃቱን ባደረሱበት ቦታ የሚገኘውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ ማእከል አቃጥለውታል፡፡ ቦኩ ሀራም እና አጋሩ የሆነው ኢስላሚክ ስቴት ዌስት አፍሪካ የተባለው ታጣቂ ቡድን ጥቃቱን በጋራ የፈፀምነው እኛ ነን በማለት ሀላፊነቱን ወስደዋል፡፡ ታጣቂዎቹ ጥቃቱን ከማድረሳቸው አስቀድመው ከመንግስት ወታደሮች እና ከእርዳታ ሰራተኞች ጋር እንዳይተባበሩ የሚያስጠነቅቅ ደብዳቤ በትነው እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ለመገናኛ ብዙሀን ተናግረዋል፡፡ ባለፉት አስር ዓመታት 100 ሺህ የሚሆኑ የሞንጉኖ ነዋሪዎች በቦኩሀራም ጥቃት ሳቢያ መኖሪያ ቀያቸውን ጥለው መሰደዳቸው ይታወሳል፡፡