በአለም የመጀመሪያውን ከመጠን ያለፈ ውፍረትን ለመቆጣጠር የሚረዳ በጨጓራ ላይ የሚታሰር ቀለበት የፈለሰፉት ፕ/ር ምትኩ በላቸው ከዚህ አለም በሞት ተለዩ::
በአለም የመጀመሪያውን ከመጠን ያለፈ ውፍረትን ለመቆጣጠር የሚረዳ በጨጓራ ላይ የሚታሰር ቀለበት የፈለሰፉት ፕ/ር ምትኩ በላቸው ከዚህ አለም በሞት ተለዩ::ታዋቂው የቀዶ ህክምና እስፔሻሊስት ፕሮፌሰር ምትኩ በላቸው በምእራብ ሸዋ ወንጪ የተወለዱ ሲሆን እድሚያቸዉ 12 አመት ሲሞላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ትምህርታቸዉን ተከታትለዋል፡፡ ፕ/ር ምትኩ ትምህርታቸዉን ሲከታተሉ ከነበረበት የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዉጪ የትምህርት እድል አጊኝተዉ ወደ ቤልጂየም በማቅናት የህክምና ትምህርታቸዉን ተከታትለዉ በአለማችን አንቱ ከተባሉ የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስቶች ተርታ መሰለፍ ችለዋል፡፡
ፕ/ር ምትኩ በአለም የመጀመሪያውን ከመጠን ያለፈ ውፍረትን ለመቆጣጠር የጨጓራ ቀለበት ወይም ጋስትሪክ ባንዲንግ ላፓሮስኮፒ የፈለሰፉ ብቸኛ አለም አቀፍ ምሁርም ነበሩ፡፡ ፕ/ር ምትኩ ከእረኝነት እስከ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስትነት በሚል ርእስ በፈረንሳይኛ ቋንቋ መፅሃፍ አሳትመዉ የነበረ ሲሆን ይህ መፅሃፍም ወደ አማሪኛና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች ተተርጉሟል፡፡ መፅሃፉ እስከ 12 ዓመት ዕድሜው ድረስ በኢትዮጵያ ተራራማ ገጠሮች እረኛ ስለነበረው
እና በኋላም ከዓለም እውቅ የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች አንዱ ስለሆነው ፕ/ር ምትኩ በላቸው ፣ አስገራሚ የሕይወት ታሪክ ይተርካል።
ከዚህም ባሻገር ፕ/ር ምትኩ በላቸው በኢትዮጵያ የተወለዱባት ወንጪ ከተማን ጨምሮ በትምህርትና በጤናዉ ዘርፍ ላይ የበጎ አድራጎት ተግባር ፈፅመዋል፡፡
ፕ/ር ምትኩ በላቸው በሚኖሩበት ቤልጂየም ሊየዥ ከተማ ባደረባቸዉ ድንገተኛ ህመም በትናንትናዉ እለት በተወለዱ በ79 አመታቸዉ ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡ አርትስ ቴሌቪዥን በፕ/ር ምትኩ በላቸው ህልፈት የተሰማዉን ሃዘን በመግለፅ ለወዳጅ ዘመዶቻቸዉ መፅናናትን ይመኛል፡፡