loading
በአዲስ አበባ በትናትናው እለት በተከሰተው የእሳት አደጋ የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ፡፡

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2014 በአዲስ አበባ በትናትናው እለት በተከሰተው የእሳት አደጋ የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ፡፡ አዲስ አበባ አደጋና ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ እንደተናገሩት ÷ በመዲናዋ በትናንትናው ዕለት ሁለት የእሳት አደጋዎች ደርሰዋል፡፡
አንዱ የእሳት አደጋ ትናንት 11 ሰዓት ከ50 ላይ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 በመኖሪያ ቤት ላይ የደረሰ ሲሆን ÷ 100 ሺህ ብር የሚገመት የንብረት ውድመት አድርሷል፡፡


ኮሚሽኑ ጥሪ እንደደረሰው የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎችን እና ሠራተኞችን ወደ ቦታው መላኩን የገለፁት ባለሙያው፥ በዚህም አደጋው የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡ በዚህም 200 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት ማዳን መቻሉን ገልፀው የሰው ሕይወት ላይም ጉዳት አለመድረሱን አመላክተዋል። ሌላኛው የእሳት አደጋ ከምሽቱ 8 ሰዓት ከ 42 ላይ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በአራት የንግድ ሱቆችና በአንድ ፔኒሲዮን ላይ የደረሰ ነው ብለዋል፡፡


በአደጋው በፔኒሲዮኑ አልጋ ተከራይተው የነበሩ 2 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፥ 200 ሺህ ብር የሚገመት ንብረትም ወድሟል። በተደረገው ርብርብ 3 ሰዎችን እንዲሁም 10 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ማዳን መቻሉን ነው ባለሙያው የተናገሩት፡፡ የአደጋዎቹ መንስዔ በመጣራት ላይ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ አቶ ንጋቱ ማሞ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት ለሚሰጡት ማህበረሰብ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉና ተገልጋዮችም አካባቢውን ማጣራት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ እንዲሁም የአየር ፀባዩ ፀሐያማና ነፋሻማ በመሆኑና ለእሳት አደጋ መባባስ አስተዋፅኦ የሚያደርግ በመሆኑ ነዋሪው ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደረግ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ፋና ዘግቧል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *