በአዲስ አበባ ትላንት በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ከአንድ ቤተሰብ 5 ሰዎች ህይወታቸዉ አልፏል-ተጎጂዎች
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 12፣2013 በመዲናዋ ትናንት በተከሰተ የጎርፍ አደጋ እስካሁን የ7 ሰዎች ህይወት አለፈ:: የአዲስ አበበ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰለሞን ፍሰሃ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በተከሰተው አደጋ በህይወት እና ንብረት ላይ የደረሱ ጉዳቶች እየተጣሩ ነው፡፡ እስካሁን በአደጋው የ7 ሰዎች ህይወት ማለፉን የገለጹት ኮሚሽነሩ÷አጠቃላይ የደረሰው ጉዳት ዛሬ ከሰዓት ይፋ እንደሚደርግም ጠቁመዋል፡፡
በመካነየሱስ ሴሚናሪ ግቢ ዉስጥ ጉዳት የደረሰባቸዉ ለአርትስ እንደተናገሩት ከአንድ ቤተስብ 5 ሰዎች በጎርፍ አደጋው ህይወታቸው አልፏል፡፡ በመዲናዋ የጎርፍ አደጋ ተከስቶ በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት ከልቤ አዝኛለሁ ሲሉ የአዲሰ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ መልዕክት አስተላልፈዋል። በአስኮ፣ በአደይአበባ፣ በጀርመን አደባባይና በጎልፍ ክለብ አካባቢ በደረሰው ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ትላንት መንገዶች ጭምር የተዘጋጉ ሲሆን፣የድንገተኛና የእሳት አደጋ ሰራተኞች በቦታዎቹ በመገኘት የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸዉ ተገልጿል፡፡
ተጎጂዎችንም ወደ ህክምና መስጫ በማጓጓዝ እና የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ እንዲያገኙ ጥረት መደረጉ ተገልጿ፡፡ የከተማው አስተዳደር ከክረምቱ ማየል ጋር ተያይዞ አስቀድሞ የመከላከል ስራዎችን እየሰራ የነበረ ቢሆንም የትላንት አደጋ ተጨማሪ ስራዎችን መስራት እንደሚገባ ያመላከተ ነው። አሁንም መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በመጪዎቹ ቀናት ከፍተኛ መጠን ያለው የዝናብ ስርጭት ስለሚኖር ነዋሪዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንድታደርጉ አደራ እላለሁ ሲሉ ወ/ሮ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት አሰተላልፈዋል።