loading
በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ፋሲል እና ባህር ዳር ከነማ አሸነፉ

አርትስ ስፖርት 28/01/2011
ሁለተኛ ቀኑን የያዘው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ትናንት (እሁድ) በምድብ ለ ቡድኖች መካከል ተካሂዷል፡፡
በዚህም በምድቡ ቀዳሚው ጨዋታ በባህርዳር ከነማ እና ወላይታ ድቻ አመካኝነት የተካሄደ ሲሆን ወደ ፕሪምየር ሊጉ አዳጊ የሆነው ቡድን ባህር ዳር ከነማ 2 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ለጣናው ሞገድ የድል ግቦችን ኤልያስ አህመድ እና ጃኮ አራፋት በሁለተኛው አጋማሽ ያስቆጠሩ ሲሆን ቡድኑ በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው እየተመራ የውድድሩን የመጀመሪያ ሶስት ነጥብ ማሳካት ችሏል፡፡
በዚህ ጨዋታ የባህር ዳር ከነማው ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ኮከብ ተብሎ ተመርጧል፡፡
ከባህር ዳር እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ከምድቡ ፋሲል ከነማ እና ጅማ አባ ጅፋር ጨዋታቸውን አከናውነዋል።
ከጨዋታው ጅማሮ በፊት የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ለቀድሞ የክለቡ ተጫዋቾች አሁን በጅማ ለሚገኙት (ሄኖክ ገምቴሳ፣ ከድር ኸይረዲን፣ ይሳቅ መኩሪያ እና ኤርሚያስ ሃይሉ) የማስታወሻ ስጦታ አበርክተውላቸዋል።
በጨዋታው ፋሲል ናይጀሪያዊው አጥቂ ኢዙ አዙካ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ታግዞ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት መርታት ችሏል፡፡
የጅማ አባ ጅፋርን ብቸኛ ግብ ቢስማርክ አፒያ አስቆጥሯል፡፡
በጨዋታው የአፄዎቹ ግብ ጠባቂ ማሊያዊው ሚኬል ሳማኬ ባሳየው አቋም ኮከብ ተብሎ ተመርጧል።
የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች በመጭው ዕሮቡ ሲቀጥል በምድብ ሀ በ9፡00 አዳማ ከተማ ከ መከላከያ እንዲሁም በ11፡00 ኢትዮጵያ ቡና ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ይጫወታሉ፡፡
ምድቡን ቡና እና ኤሌክትሪክ በእኩል ሶስት ነጥቦች ይመራሉ፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *