በአፍሪካ በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ100 ሺህ በላይ መድረሱ ተነገረ፡፡
አዲስ አበባ፣የካቲት 12፣ 2013 በአፍሪካ በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ100 ሺህ በላይ መድረሱ ተነገረ፡፡ በአህጉሩ የተመዘገበው የሟችና የታማሚዎች ቁጥር ከቀሪው ዓለም ጋር ሲነፃፀር አናሳ ቢሆንም የበሽታው ስርጭት ከነበረበት በፍጥነት እየጨመረ ነው ተብሏል፡፡ በተለይ በአፍሪካ ሁለተኛው ዙር የወረርሽኝ መስፋፋት መከሰቱን ተከትሎ ሆስፒታሎች በሽተኞችን መቀበል እስኪያቅታቸው መጨናነቃቸው ነው የሚነገረው፡፡
አልጀዚራ እንደዘገበው በአፍሪካ በሽታው ከታየ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ባለው ጊዜ 100 ሺህ 354 ሰዎች ህይዎታቸው ማለፉ ተረጋግጧል፡፡ አሁን ላይ ብዙ የሞት መጠን የተመዘገበው በደቡባዊው የአፍሪካ ክፍል እንደሆነ በርካታ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ በአፍሪካ በቫይረሱ ከሚያዙት ሰዎች መካከል የሟቾች መጠን በመቶኛ ሲሰላ 2 ነጥብ 6 በመቶ ሲሆን ይህም አህጉሪቱ ካላት የታማሚዎች ቁጥር አንፃር ሲታይ ከፍተኛ መሆኑ ይነገራል፡፡
በአፍሪካ የኮሮናቫይረስ ታማሚዎችና የሟቾች ቁጥር አንሶ መታየቱ የሀገራቱ የመመርመር አቅም ደካማ በመሆኑ የተነሳ ነው የሚል አስተያየት ይበዛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ ተቋማት በአፍሪካ የክትባት አገልግሎት በፍጥነት እንዲዳረስና በሽታውን መከላከል አንዲቻል ደጋግመው ጥሪ እያቀረበቡ ይገኛሉ፡፡