በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዋልያዎቹ በኬንያ አቻቸው ሽንፈት አስተናገ ዱ
አርትስ ስፖርት 04/02/2011
ለ2019ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ለማለፍ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) የምድብ አራተኛ ጨዋታቸውን በናይሮቢ ካዛራኒ ስታዲየም ከኬንያ አቻው ጋር አካሂዶ ሽንፈት አስተናግዷል፡፡
ዛሬ ቀን 10፡00 ሁለቱ ቡድኖች ባደረጉት ጨዋታ ኬንያ በሚካኤል ኦሉዋንጋ፣ ኤሪክ ዮሃና በጨዋታ እንዲሁም የቡድኑ አምበልና የቶትናሀሙ አማካይ ቪክቶር ዋንያማ በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥረው 3 ለ 0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችላለች፡፡
በጨዋታው ዋልያዎቹ በአጠቃላይ እንደ ቡድን መጥፎ የጨዋታ እንቅስቃሴ የነበራቸው ሲሆን ያልተደራጀ ቡድን እንደነበረ መመልከት ተችሏል፡፡
የሀራምቤ ስታርስ ከዋልያዎቹ በላቀ የማሸነፍ ስሜት የነበራቸው፤ ጫና መፍጠር የቻሉበት ሲሆን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአንፃሩ ቅንጅት የሚጎድለው፣ በሀይል ኳስን ለመቆጣጠር መሞከር እና የትኩረት ማነስ የነበረበት፤ የሚጠቀስ የጎል ሙከራ እንኳ በወጉ ማድረግ አልቻሉም፡፡ የኬንያው ግብ ጠባቂ ፓትሪክ ማታሲም ስራፈት ሁኖ የጨረሰበት ጨዋታ ነበር፡፡
ኬንያም ከጨዋታ ብልጫ ጋር ማሸነፍ ችላለች፡፡ ይህን ተከትሎ ምድቡን በሰባት ነጥብ መምራቷን አጠናክራለች፡፡ ዋልያዎቹ ደግሞ በአራት ነጥብ ይከተላሉ፡፡ ጋና እና ሴራሊዮን ደግሞ በተመሳሳይ ሶስት ነጥብ ተከታዮቹን ደረጃዎች መያዝ ችለዋል፡፡