በኢትዮጵያ ሰዉ ሰራሽና ተፈጥሮ አመጣሽ ችግር ሳቢያ የአረጋዉያን አኗኗር ፈተና ላይ እየወደቀ ነዉ
አርትስ 28/02/2011
ዛሬ በኢትዮጵያ ለ27ኛና በአለም ለ28ኛ ግዜ በተከበረዉ የአረጋዉያን ቀን ላይ የኢፌዴሪ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደተናገሩት አረጋዉያን አሁን ያለንን ቁሳዊና መንፈሳዊ ሃብት ካለፈዉ ትዉልድ ተረክበዉ ፤የራሳቸዉንም ጨምረዉ ዛሬ ያደረሱን ቢሆንም የሚገባቸዉን ክብር አላገኙም ብለዋል፡፡
አሁንም በተለያዩ ሰዉ ሰራሽና ተፈጥሮ አመጣሽ ችግር ሳቢያ የአረጋዉያን አኗኗር ፈተና ላይ እየወደቀ በመሆኑ ባለመታከት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል ሚኒስትሯ፡፡
ከዚህም ሌላ በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች እየተከሰቱ ያሉ የጥፋት ድርጊቶች እንዲታረሙና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ያላቸዉን እምቅ እዉቀትና ጥበብ በመጠቀም ያለመታከት እንዲሰሩ ዶ/ር ኤርጎጌ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአሉ “ቀደምት የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾችን በመዘከር የኢትዮጵያ አረጋዉያንን ተሳትፎና ተጠቃሚነት እናረጋግጥ “በሚል መሪ ቃል ተከብሮ ዉሏል፡፡