በኢትዮጵያ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 16 ሚሊየን ከፍ አለ::
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2012 በኢትዮጵያ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 16 ሚሊየን ከፍ አለ::በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በኢትዮጵያ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 16 ነጥብ 5 ሚሊየን ከፍ ማለቱን በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፅህፈት ቤት አስታወቀ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከኢትዮጵያ መንግስት እና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር የ2020 የሰብዓዊት እርዳታ ፍላጎቶች ላይ ክለሳ አድርጓል።
በፈረንጆቹ 2020 ጥር የወጣ ሪፓርት በኢትዮጵያ ምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ያልሆነ የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው 7 ሚሊየን ሰዎች መሆናቸው መነገሩ ይታወሳል። ሆኖም የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ባሳደረው ጫና ምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ያልሆነ የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 16 ነጥብ 5 ሚሊየን ከፍ ማለቱን ድርጅቱ አስታውቋል። ለ16 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች የሚያስፈልገውን ምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ያልሆነ ድጋፍ ለማቅረብ 1 ነጥብ 6 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግም ነው የተነገረው። 9 ነጥብ 8 ሚሊየን የሚሆኑት ሰዎች የሰብዓዊ እርዳታ ሊያስፈልጋቸው የቻለው በኮሮና ቫይረስ ምክንያት መሆኑን ነው ድርጅቱ የገለፀው። ለእነዚህም ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላሩ መካከል 506 ሚሊየን ዶላሩ ምግብ ነክ እና
ምግብ ነክ ያልሆነ ድጋፎችን ለማድረግ ይውላል ተብሏል።