loading
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና መሪነቱን ያስጠበቀ ድል ሲያሳካ፤ ጊዮርጊስ ደረጃውን አሻሽሏል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና መሪነቱን ያስጠበቀ ድል ሲያሳካ፤ ጊዮርጊስ ደረጃውን አሻሽሏል

የ11ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ትናንት መካሄድ ጀምረዋል፡፡

በሊጉ አናት ላይ የተቀመጠው ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አበባ ስታዲየም ሀዋሳ ከነማን አስተናግዶ ነበር፤ ሁለቱ ቡድኖች በደረጃ ሰንጠራዡ አንደኛና ሁለተኛ ላይ መገኘታቸው ግጥሚያውን ተጠባቂ አድርጎታል፡፡

በዲዲዬ ጎሜስ ዳሮሳ የሚመራው ቡና ጨዋታውን በ1 ለ 0 ጠባብ ውጤት ድል አድርጓል፡፡ ቡናማዎቹ ከራሳቸው የሜዳ ክልል መስረተው ወደ ተጋጣሚያቸው ቡድን በጥሩ ቅብብል ይዘው በመምጣት ከግራ መስመር የኋላሸት ፍቃዱ ያሻገራትን የአየር ላይ ኳስ ሱሌማን ሎክዋ በጨዋታው ጅማሮ ስድስተኛው ደቂቃ ላይ በግንባር ገጭቶ ማስቆጠር ችሏል፡፡

በቀሪዎቹ የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ቡናዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ቢሞክሩም ፍሬ ማፍራት ግን አልቻሉም፤ ሀዋሳዎችም አንዳንድ የሚያገኟቸውን ኳሶች በመያዝ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመግባት የሚያርጓቸው እንቅስቃሴዎች በቡና ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂ ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት የሚፈልጉትን  ጎል እንዳያስቆጥሩ እንቅፋት ሁኖባቸዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹ 25 ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች በተለይ ደግሞ ሀዋሳ ብልጫ በወሰዱባቸው የጨዋታ እንቅስቃሴዎች ጊዜ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም፡፡

የጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይም አቻ ለመሆን የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር፡፡

በአጠቃላይ ሙሉ ግጥሚያው ኃይል የቀላቀለ የጨዋታ እንቅስቃሴ የተሞላ ሲሆን ቡናማዎች እንደፈጠሯቸው የግብ ሙከራዎች  ስል የፊት መስመር ጨራሽ አጥቂ ቢኖራቸው ኖሮ  ተጨማሪ ግቦችን ማስመዝገብ በቻሉ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች በጠባብ የግብ ልዩነት እያሸነፉ ቢሆንም ዘወትር በየሳምንቱ፤ 12 ቁጥር ማሊያን ለብሶ የስታዲየሙ ግርማ ሞገስ በመሆን በዝማሬና በጭፈራ ቡድኑን እያበረታ የሚገኘው ደጋፊ ማራኪ የጨዋታ እንቅስቃሴን እያስመለከቱ አይደለም ሲባሉ ነበር፡፡

በትናንቱ ድል ግን ካለፉት ግጥሚያዎች በተሻለ ቢያንስ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አሳይተውታል፡፡ ቡና አሁንም በሊጉ አናት ላይ ተቀምጦ መሪነቱን በ22 ነጥብ አስቀጥሏል፡፡

የቡናው አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ‹‹ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር፤ ብዙ ተጫዋቾች የተጎዱብን ቢሆንም አሁንም አንደኛ ደረጃ ላይ እንገኛለን። ተጫዋቾቼም ቆራጥነታቸውን በማሳየታቸው በጣም ደስ ብሎኛል። ዋናው ነገር መሪነታችንን ማስቀጠላችን ላይ ነው። ምርጡ የተከላካይ ክፍል አለን፤ ተጫዋቾቼ ያላቸውን ሁሉ ለቡና እየሰጡ ነው›› ብለዋል።

የሀዋሳ ከነማው አዲሴ ካሳ ደግሞ ‹‹ የጨዋታው መጀመሪያ ላይ ክፍተት በመፍጠራችን ግብ አስተናግደናል፤ የቡድኑንም የማጥቃት እንቅሳቃሴ ጥሩ አልነበረም ብለዋል፡፡

ትናንት ክልል ላይ በተከናወኑ ሌሎች ጨዋታዎች፤ ድሬዳዋ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬዳዋ ከነማን በሳላዲን ሰኢድ ግብ 1 ለ 0 በማሸነፍ በደረጃ ሰንጠራዡ በ18 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

ሀዋሳ ላይ ሲዳማ ቡና ደቡብ ፖሊስን 3 ለ 1 ሲያሸንፍ፤ መቐለ ላይ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ባህር ዳር ከነማን 1 ለ 0 ረትቷል፡፡

ዛሬ በከተራ ዕለት በአዲስ አበባ ስታዲየም መከላከያ ስሑል ሽረን እንዲሁም ጎንደር ላይ ፋሲል ከነማ ወላይታ ድቻን ረፋድ 4፡00 ሊል ያስተናግዳሉ፡፡

ዕሁድ ደግሞ ደደቢት በትግራይ ስታዲየም አዳማ ከተማን ይገጥማል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *