በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ሊቨርፑል በተቀናቃኙ ማንችስተር ዩናይትድ ላይ ድል ተቀዳጅቷል
አርትስ ስፖርት 08/04/2011
የ17ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በሳምቱ መጨረሻ ቀናት ተከናውነዋል፤ ትናንት ተጠባቂ ግጥሚያዎች የተደረጉ ሲሆን የሳምንቱ ከባድ ፍልሚያ በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም በሰሜን ምዕራብ ደርቢ ሊቨርፑልከ ማንችስተር ዩናይትድ ተጫውተው፤ ባለሜዳው ሊቨርፑል በተቀናቃኙ ዩናይትድ ላይ ሙሉ የጨዋታ ብልጫ በመውሰድ ጣፋጭ የ3 ለ 1 ድል አስመዝግቧል፡፡
ለቀያዮቹ ሻኪሪ ሁለት እንዲሁም ማኔ አንዷን ግብ ሲያስቆጥሩ፤ ሊንጋርድ የቀያይ ሰይጣኖቹን ከባዶ መሸነፍ ያዳነች ጎል አስገኝቷል፡፡ ሊቨርፐል ድል ማድረጉን ተከትሎ የሊጉን መሪነት ከማንችሰተር ሲቲ ተረክቧል፡፡
ወደ ሴንት ሜሪ ያቀናው አርሰናል አዲስ አሰልጣኝ የሾሙትን ሳውዛምተንን ገጥመው ከ22 ጨዋታ ያለመሸነፍ ጉዞ በኋላ የ3 ለ 2 ሽንፈት አስተናግዷል፡፡ አርሰናል ሁለቴ እየተመራ ሁለቴ አቻ መሆን ቢችልም በመጨረሻ እጅሰጥቷል፤ ለደቡብ ጠረፉ ቡድን አስፈላጊ ሶስት ጎሎችን ዳኒ ኢንግስ ሁለት እና አውስቲን ከመረብ ሲያገናኙ እንዲሁ ለመድፈኞቹ ሄነሪክ ሚኪታሪያን ግቦቹን ከመረብ አገናኝቷል፡፡
ቼልሲ ብራይተንን በሃዛርድ እና ፔድሮ ግቦች 2 ለ 1 ረትቷል፡፡
ቅዳሜ ዕለት የፔፕ ጓርዲዮላው ማንችስተር ሲቲ ኢቨርተንን 3 ለ 1 ሲያሽንፍ ጋብሪየል ጀሱስ ሁለት ግቦችን ለቡድኑ ሲያበረክት ስተርሊንግ ቀሪዋን አስቆጥሯል፤ ቶተንሃም በኢሪክሰን የመጨረሻ ደቂቃ ብቸኛ ጎል ተፈትኖ በርንሊን1 ለ 0 አሸንፏል፡፡
በሌሎች ግጥሚያዎች ክሪስታል ፓላስ ሌስተርን፣ ኒውካስትል ሀደርስፊልድን በተመሳሳይ 1 ለ 0 ሲያሸንፉ፣ ወልቭስ በርንማውዝን፣ ዌስት ሃም ፉልሃምን በተመሳሳ 2 ለ 0 እንዲሁም ዋትፎርድ ካርዲፍ ሲቲን 3 ለ 2 አሸንፈዋል፡፡
ሊጉን ሊቨርፑል በ45 ነጥብ ሲመራ፣ ማንችስተር ሲቲ በ44 ሁለተኛ፣ ቶተንሃም በ39 ሶስተኛ፣ ቼልሲ በ37 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ፤ አርሰናል በ34 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ እንዲሁም ማንችስተር ዩናይትድ በ26 ነጥችስድስተኛ ደረጃ ላይ ተገኝተዋል፡፡