በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ቼልሲ ሽንፈት ሲገጥመው፤ ሊቨርፑል ነጥብ ጥሏል
በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ቼልሲ ሽንፈት ሲገጥመው፤ ሊቨርፑል ነጥብ ጥሏል
የ24ኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ቀሪ አራት ጨዋታዎች ትናንት ምሽት ተከናውነዋል፡፡
ቦርንመዝ በሜዳው ዲን ኮርት የምዕራብ ለንደኑን ቼልሲ አስተናግዶ 4 ለ 0 በማሸነፍ ሶስት ነጥብ ሜዳው ላይ አስቀርቷል፡፡ ቦርንመዞች አሸናፊ ያደረጓቸውን ጎሎች ጆሹዋ ኪንግ ሁለት እንዲሁም ዴቪድ ብሩክስ እና ቻርሊ ዳንዬልስ አስቆጥረዋል፡፡
ከተጫዋቾቻቸው ጋር ስምሙ እንዳልሆኑ የሚነገርላቸው ማውሪዚዮ ሳሪም አሳፋሪ ሽንፈት ገጥሟቸው በደረጃ ሰንጠራዡ አራተኛን ለኡናይ ኢምሪው አርሰናል አስረክበው ወደ አምስተኛ ዝቅ ብለዋል፡፡
መርሲ ሳይድ ላይ ደግሞ ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ሮድ ሌስተር ሲቲን አስተናግዶ በአንድ አቻ ውጤት አጠናቅቋል፡፡
ሊቨርፑል ጨዋታው በተጀመረ 121ኛው ሰከንድ ላይ፤ ሳዲዮ ማኔ ባስቆጠራት ግብ ቀዳሚ መሆን ቢችሉም፤ ቀበሮዎቹ የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት ተከላካዩ ሃሪ ማጉይር ከመረብ ባገናኛት ኳስ ቡድኑ አቻ መሆን ችሏል፡፡
በሌሎች የምሽቱ ጨዋታዎች ቶተንሃም ዊምብሌ ላይ ዋትፎርድን ገጥሞ ከኋላ ተነስቶ ባስቆጠራቸው ግቦች 2 ለ 1 ረትቷዋል፡፡
በምሽቱ ጨዋታ ክሬግ ካችካርት ለዋትፎርድ ባስቆጠራት ግብ እስከ 80ኛው ደቂቃ ድረስ 1 ለ 0 ሲመሩ ቢቆዩም፤ ከእስያ ዋንጫ የተመለሰው ሰን ሁንግ ሚን እና ፌርናንዶ ዮሬንቴ ቡድኑን ባለድል ያደረጉ ጎሎች አስቆጥረዋል፡፡
ወደ ደቡብ ጠረፍ ያቀናው የለንደኑ ክሪስታል ፓላስ ከሳውዛምፕተን ጋር በአንድ አቻ ውጤት ተለያይቷዋል፡፡
የሊጉን የደረጃ ሰንጠራዥ ሊቨርፑል በ61 ነጥብ መምራቱን ቀጥሏል፤ ማ.ሲቲ በ56 ሁለተኛ፤ ቶተንሀም በ54 ሶስተኛ፤ አርሰናል እና ቼልሲ በተመሳሳይ 47 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው፤ አራተኛና አምስተኛ እንዲሁም ማ.ዩናይትድ በ45 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ካርዲፍ፣ ፉልሃም እና ሀደርስፊልድ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ፡፡