በእግረኞች ላይ ትኩረት ያደረገ የአሥር ዓመታት የመንገድ አጠቃቀም ስትራቴጂ ይፋ ተደረገ
በእግረኞች ላይ ትኩረት ያደረገ የአሥር ዓመታት የመንገድ አጠቃቀም ስትራቴጂ ይፋ ተደረገ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ነው ስትራቴጂውን ይፋ ያደረገው፡፡
በከተማዋ የትራንስፖርት አጠቃቀም 15 በመቶ የቤት መኪና፣ 34 በመቶ የሕዝብ ትራንስፖርት እንደሆነ ያስታወቀው ቢሮው፣ 54 በመቶ የሚሆነው ነዋሪ እግረኛ ሆኖ ሳለ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ ተግባራዊ ይደረግ የነበረው አሠራር ብዙኃኑን ያገለለ ነበር ተብሏል፡፡
አዲስ ስትራቴጂ ማውጣት ያስፈለገውም የብዙኃኑን ነዋሪ ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል አሠራር ለማምጣት መሆኑን አስታውቋል፡፡
ሞተር አልባ ትራንስፖርት በሚል የቀረበው ስትራቴጂ ለእግረኞችና ለብስክሌት ተጠቃሚዎች ምቹ መንገዶችን ማዘጋጀት ላይ ያተኮረ እንደሆነ፣ ምክትል ከንቲባው ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ ገልጸዋል፡፡
600 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ ነባርና አዳዲስ መንገዶች ጥራት ያላቸው የእግረኛ መንገዶችን፣ ደኅንነታቸው የተጠበቁ ማቋረጫዎችንና በቂ የመንገድ ዳር መብራቶችን እንዲያካትቱ ማድረግ፣ የስትራቴጂው አካል መሆኑ ተገልጿል፡፡
ከፍተኛ የእግረኛ እንቅስቃሴዎች ባሉባቸው እንደ መገናኛ፣ መርካቶ፣ ፒያሳና ቸርችል ጎዳና ባሉ ሥፍራዎች ደረጃቸውን የጠበቁ የእግረኛ መንገዶች፣ የእግረኛ ማቋረጫዎችና የሕዝብ መገልገያ ቦታዎችም ይገነባል ተብሏል፡፡
ስትራቴጂው የኮንዶሚኒም ፕሮጀክቶች፣ የተጠጋጉ የቤት ንድፎችና የሞተር አልባ ትራንስፖርት ተደራሽነትን ያማከለ የሕዝብ ትራንስፖርት ኮሪደሮችን እንዲካተትም ያስገድዳል ነው የተባለለው ሪፖርተር እንዳስነበበው፡፡