በካሊፎርኒያ የተቀሰቀሰው ሰደድ እሳት በሽዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ሲያፈናቅል የአንድ ሰው ህይዎት ማለፉ ተሰምቷል::
አዲስ አበባ፣ነሐሴ 14፣ 2012 በካሊፎርኒያ የተቀሰቀሰው ሰደድ እሳት በሽዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ሲያፈናቅል የአንድ ሰው ህይዎት ማለፉ ተሰምቷል:: አልጀዚራ በዘገባው እንዳስነበበው በእሳት አደጋው ህይዎቱ ያለፈው ግለሰብ በስራ ላይ የተሰማራ የእሳት አገደጋ ሰራተኛ ነው፡፡ እሳቱ ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ በሚሸፍን ቦታ ላይ ከፍተኛ ጥፋት ማድረሱን የግዛቲቱ ባለ ስልጣናት ተናግረዋል፡፡ የካሊፎርኒያ ግዛት አስተዳዳሪ ጋቪን ኒውሰም እንዲህ አይነት የከፋ አደጋ ከብዙ ዓመታት ወዲህ ገጥሞን አያውቅም ብለዋል፡፡
የግዛቷ የእሳት አደጋ መከላከል እደና ደን ጥበቃ ተቋማት በሰጡት መግለጫ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ ግዴታ ውስጥ ገብለዋል ነው ያሉት፡፡ ፖሊሶችና የእሳት አደጋ ሰራተኞች ነዋሪዎቹ ራሳቸውን ከአደጋው እንዲያድኑ የቤት ለቤት ማስጠንቀቂያ ማድረግ ግድ እንደሆነባቸውም ዘገባው አመላክቷል፡፡ ካሊፎርኒያ በ10 ዓመት ውስጥ ከ370 በላይ የእሳት አደጋዎች የተከሰቱባት ሲሆን ከነዚህም መካከል ከደርዘን በላይ የሚሆኑት ትልቅ ውድመት ያደረሱ ናቸው ተብሏል፡፡